ቀጥታ፡

የአደጋ ስጋት አመራር ስራን በራስ አቅም ለመሸፈን ሰፊ ጥረት እየተደረገ ነው-አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 3/2016(ኢዜአ)፦የአደጋ ስጋት  አመራር ስራን በራስ አቅም ለመሸፈን ሰፊ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር) ገለጹ።

በአሁን  ጊዜ አዲስ አበባና ድሬዳዋ አስተዳደሮችን ጨምሮ ስድስት ክልሎች ከፌዴራል መንግስት ምንም አይነት ሰብዓዊ ድጋፎችን አይቀበሉም ብለዋል።

የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር) በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል።

በዚሁ ጊዜ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ስራን ከልመናና ከተረጂነት ለማላቀቅ ከንድፈ ሀሳብ ባለፈ ሰፊ ጥረት እየተደረገና ተጨባጭ ውጤቶች እየተመዘገቡ ነው ብለዋል።

ህብረተሰቡን በማሳተፍ የሚከናወኑ የሰብዓዊ ድጋፍ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸው የአገርን ክብርና ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ጉልህ ሚና እንዳላቸው ነው ኮሚሽነሩ ያብራሩት፡፡

በ2016 በጀት ዓመት ብቻ ምግብን ገዝቶ ለማከፋፈል ከ47 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉን አስታውሰው፣ ህብረተሰቡን በማስተባበር በቁርጠኝነት ቢሰራ ወጪውን ከግማሽ በታች መቀነስ ይቻል ነበር ብለዋል።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከአምስት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ኩንታል በላይ ስንዴ በመግዛት ለስድስት ነጥብ አምስት ሚሊየን ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ ማድረግ መቻሉንም ነው ያብራሩት።


 

ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለመሸፈን የሚደረገው ጥረት ከንድፈ ሀሳብ ባለፈ ወደ ተግባር እየተቀየረ መሆኑንም ነው ኮሚሽነሩ ያብራሩት።

ለአብነት አዲስ አበባና ድሬዳዋ አስተዳደሮችን ጨምሮ ስድስት ክልሎች በአሁን ጊዜ ምንም አይነት ሰብዓዊ ድጋፍ ከፌዴራል መንግስት አለመውሰዳቸው ትልቅ ስኬት ነው ብለዋል።

የክረምቱ ዝናብ እያየለ መምጣቱን ተከትሎ የአደጋ ስጋትን ቀድሞ ለመከላከል በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም አምባሳደር ሽፈራው አንስተዋል።

የጎርፍ አደጋ ፣የመሬት መንሸራተት፣ የተለያዩ ወረርሽኞች ሊከሰቱ ስለሚችሉ ለምላሹ ቀድሞ መዘጋጀት ይገባል ብለዋል።

በዚህ ምክንያት 800 ሺ ያህል ዜጎችን ሊያፈናቅል የሚችል የአደጋ ስጋት መኖሩን ኮሚሽነሩ የጠቀሱ ሲሆን ቀድሞ የመከላከል ተግባሩን በጋራ ማከናወን አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።

 

 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም