ቀጥታ፡

በቡና ምርትና ግብይት ላይ ያሉ ችግሮችን በተቀናጀ መልኩ በመቅረፍ ኢንዱስትሪውን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ እየተሰራ ነው - ማህበሩ 

ሀዋሳ፤ ሐምሌ 3/2016 (ኢዜአ) ፡-ከመንግስት ጎን በመሆን በቡና ምርትና ግብይት ላይ ያሉ ችግሮችን በተቀናጀ መንገድ በመቅረፍ ኢንዱስትሪውን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ የቡና ማህበር ገለፀ ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የቡና ማህበር ለአባላቱ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናና የውይይት መድረክ በሀዋሳ ከተማ አካሄዷል።

የማህበሩ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ዘሪሁን ቃሚሶ እንደገለፁት፤ ቡና ለሀገር ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪን የሚያስገኝ ሆኖ ሳለ የምርት እንዲሁም የግብይት ሥርዓቱ ትኩረት በመነፈጉ ሳቢያ ዘርፉ በችግሮች ውስጥ እያለፈ መጥቷል።

በዘርፉ ትርጉም ያለው ለውጥ ለማምጣት መንግስት በወሰዳቸው የማሻሻያ እርምጃዎች ለውጦች መታየት መጀመራቸውን አቶ ዘሪሁን ተናግረዋል።

ማህበሩ ከመንግስት ጎን በመሆን የቡና ምርትና ግብይት ላይ ያሉ ችግሮችን ከመሰረታቸው በመፍታት የቡና ኢንዱስትሪውን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ የተለያዩ ሥራዎችን እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

ማህበሩ ከዘርፉ መስሪያ ቤቶች ጋር በመተባበር የቡናና ቅመማ ቅመም ኤግዚቢሽን ከማዘጋጀት ጀምሮ ሌሎች ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልፀው ከዲላ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበርም የተለያዩ ምርምሮችን እያካሄደ እንደሚገኝም አስረድተዋል።


 

የሲዳማ ክልል ቡናና ቅመማ ቅመም ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መስፍን ቃሬ ቡና ለበርካታ ዓመታት ተገቢ የሆነ ድጋፍና የኤክስቴንሽን አገልግሎት ያልተሰጠው ዘርፍ ከመሆኑም ባሻገር ግብይቱንም ደላሎችና ጥቂት ግለሰቦች የሚዘውሩት ሆኖ መቆየቱን ተናግረዋል።

በዚህም ሁኔታውን ለመቀየር መንግስት በጀመረው የሪፎርም ሥራ ለውጦች እየመጡ እንደሆነ ገልፀው በሪፎርሙም ሁለትና ከዚያ በላይ ሄክታር የቡና ማሳ ያላቸው አርሶ አደሮች፣ አልሚ ባለሀብቶች እንዲሁም አቅራቢና ላኪ ነጋዴዎች ምርታቸውን በቀጥታ ለውጭ ገበያ ማቅረብ እንዲችሉ መደረጉን አውስተዋል።


 

በሲዳማ ክልል ምስራቃዊ ዞን ቦና ዙሪያ ወረዳ በቡና አቅራቢነት የተሰማሩት አቶ ኤጋታ ቡሼ የማህበሩ መደራጀት ጥቅሙ ለሁሉም መሆኑን አንስተው በተለይ በግብይት ሰንሰለት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመቅረፍ በቡና ዙሪያ ያሉ ተዋናዮችም ሆኑ አገሪቷ ተጠቃሚ ሊሆኑ እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

በመድረኩ ላይ ከሲዳማ ክልልና ከኦሮሚያ ክልል የተወሰኑ ዞኖች የተውጣጡ የቡና አቅራቢዎች፣ ላኪ አርሶ አደሮችና የሚመለከታቸው አካላት ተገኝተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም