ኮሌጁ የተሻሻሉ የቡና፣ ፍራፍሬና ቅመማቅመም ዝርያ ችግኞችን የማላመድና የማስፋፋት ስራ እያከናወነ መሆኑን ገለጸ

ሚዛን አማን፤ ሀምሌ 3/2016 (ኢዜአ)፦የሚዛን ግብርና ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኮሌጅ በምርምር የተገኙ የተሻሻለ ዝርያ ያላቸው የቡና፣ፍራፍሬና ቅመማቅመም ችግኞችን እያላመደና እያስፋፋ መሆኑን  አስታወቀ፡፡

በምርምር የተገኙ ምርጥ የፍራፍሬና የቡና ዝርያ ችግኝ ዝግጅት ሥራ ያለበት ደረጃን ለመገምገም ያለመ የመስክ ምልከታ ዛሬ በኮሌጁ ዘር ብዜት ጣቢያዎች ተካሂዷል።


 

የኮሌጁ ዲን አቶ ካሳሁን ናይክን በወቅቱ እንደገለጹት ኮሌጁ በግብርና ዘርፍ በምርምር የተገኙ ውጤቶችን በአካባቢው ለማስፋፋት እየሰራ ነው፡፡

ለዘንድሮ የክረምት ወራት የሚተከሉ ከ550 ሺህ በላይ ዝርያቸው የተሻሻለ ምርጥ የቡናና የፍራፍሬ ችግኞች መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

ከችግኞቹ ውስጥ 400 ሺህ ያህሉ በሽታ የሚቋቋሙና ምርታማ የቡና ችግኞች መሆናቸውን ጠቅሰው የቡና ችግኞቹ "የጌሻ ቡና"፣ "ሰባ አራት አርባ" እና "ሰባ አራት ሃምሳ አራት" የተሰኙ ምርጥ የቡና ዝርያ ያላቸው መሆናቸውን  ጠቅሰዋል።

"ችግኞቹን ለአርሶ አደሮች በማሰራጨት ምርትና ምርታማነቱ የተረጋገጠ ቡና እንዲለማ ይደረጋል" ብለዋል።

ከቡና ባሻገር በሁለት ዓመት ውስጥ ምርት የሚሰጥ የአቡካዶ፣ ቁንዶ በርበሬ፣ ሻይ ቅጠል እንዲሁም ሌሎች ፍራፍሬዎችና ቅመማ ቅመሞችን የማላመድና የማስፋፋት ሥራ ላይ ትኩረት መደረጉን ገልጸዋል።


 

ዲኑ አክለውም ኮሌጁ የምርምር ሥራዎችን ከቴፒ ግብርና ምርምር ማዕከል ጋር በመተባበር እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል ።

በማባዣ ችግኝ ጣቢያዎችም ከሀምሳ ለሚበልጡ ወጣቶች በስልጠና የታገዘ የሥራ ዕድል መፈጠሩን ጠቁመዋል።

በኮሌጁ የቴክኖሎጂ ብዜትና ኢንተርፕራይዝ ልማት ምክትል ዲን ዋለልኝ ዓለምነህ በበኩላቸው ኮሌጁ የመንግስትን የልማት ፖሊሲ የተከተለ የልማት ሥራን ለማቀላጠፍ  ጥረት እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

የእንስሳትና ንብ እርባታ ሥራን ጨምሮ በምርምር የተደገፉ ተግባራትን በአርሶ አደሩ ማሳ በማላመድ እየተወጣ ያለውን ማኅበራዊ ኃላፊነት አጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል።

" ኮሌጁ  በቀጣይየራሱን ገቢ ለማመንጨት በሚያከናውናቸው ተግባራት ለበርካቶች የሥራ ዕድል በመፍጠር የቴክኖሎጂ ሽግግር ያደረጋል" ብለዋል።

የቤንች ሸኮ ዞን ቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሪት ወርቅነሽ ባድንስ ኮሌጁ የምርምር ውጤቶችን በአካባቢው ለማላመድ እያደረገ ያለው ጥረት የአርሶ አደሩን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ከፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

የነባር ዝርያዎች ምርታማነት እያሽቆለቆለ መምጣቱን ጠቅሰው በቀጣይ በምርምር የተገኙ ዘሮችን ይበልጥ ለማስፋፋት ከኮሌጁ ጋር ተቀናጅተው እንደሚሠሩ አመላክተዋል።

በኮሌጁ የተሻሻሉ የችግኝ ዘሮችን ማባዛት ላይ የሥራ ዕድል ከተፈጠረላቸው መካከል ወጣት ሙላቱ ዳባ ራሱን ለማስተዳደር የሚያስችል ገቢ እያገኘ መሆኑን ተናግሯል።

በችግኝ ዝግጅት ሥራ ላይ ከተሰማራ አንድ ዓመት እንደሆነው ገልጾ ከገቢ ባሻገር ያዘጋጃቸው ችግኞች ለውጤት ሲበቁ ማየት እንደሚያስደስተው ገልጿል።


 

በችግኝ ጣቢያው የሥራ ዕድል የተፈጠረለት የኮሌጁ ተመራቂ ወጣት ዓለማየሁ መኮንን በበኩሉ የተሻለ ልምድና ክህሎት እያዳበረ መሆኑን ገልጿል።

የሚዛን ግብርና ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኮሌጅ ከ1994 ዓ.ም ጀምሮ ተማሪዎችን በመቀበል የግብርና ባለሙያዎችን ከማፍራት ባሻገር በግብርናው ዘርፍ ምርምሮችን እያደረገ የሚገኝ ኮሌጅ ነው።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም