ለህብረተሰቡ ግልጽና ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት ለዘላቂ ሰላም መስፈን የድርሻችንን እንወጣለን -የመንግስት ሰራተኞች

ደብረ ብርሀን ፤ሐምሌ 3/2016 (ኢዜአ)፦ ለህብረተሰቡ ግልጽና ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠትና መልካም አስተዳደርን በማፋጠን ለዘላቂ ሰላም መስፈን የድርሻችንን እንወጣለን ሲሉ  የደብረ ብርሀን ከተማ አስተዳደር የመንግስት ሰራተኞች ገለፁ።

የደብረ ብርሀን ከተማ አስተዳደር የመንግስት ሰራተኞች "ሰላም ለሁሉም፤ ሁሉምለሰላም" በሚል መሪ ሃሳብ ዛሬ የሰላም ኮንፍረንስ አካሂደዋል።

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል አቶ ደበበ እሸቴ እንደገለጹት፤ መንግስት በክልሉ ሰላምን በዘላቂነት ለማረጋገጥ የሰላም ውይይት ማዘጋጀቱ አስደሳች ነው ።

ለህዝቡ ቀልጣፋና ግልጽ አገልግሎት በመስጠትና መልካም አስተዳደርን በማፋጠን ለዘላቂ ሰላም መስፈን የበኩላቸውን እንደሚወጡም ተናግረዋል ።

ሌላው የመንግስት ሰራተኛ አቶ ዳዊት አሰፋ በበኩላቸው፤ መንግስት ችግሮችን በውይይት በመፍታት ለዘላቂ ሰላም መስፈን የሚያደርገው ጥረት የሚበረታታ መሆኑን አመልክተዋል።

"ባንጻሩ ሰላምን የማይፈልጉ አንዳንድ ግለሰቦች በማህበራዊ ሚዲያ ከሚያስተላልፉት የተሳሳተ ትርክት ሊቆጠቡ ይገባል" ብለዋል።

በተሰማሩበት የሙያ ዘርፍ ህዝብን በቅንነትና ታማኝነት በማገልገል ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የድርሻቸውን ለመወጣት እንደሚጥሩም አብራርተዋል።

የደብረ ብርሀን ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ በድሉ ውብሸት በበኩላቸው፤ "የከተማው ሰላም የተጠበቀ በመሆኑ የንግድና ኢንቨስትመንት ስራዎች ሳይቋረጡ ቀጥለዋል" ብለዋል።

ለዚህም የከተማው ነዋሪዎችና የመንግስት ሰራተኞች ከፍተኛ ሚናቸውን መወጣታቸውን ጠቅሰው፤ ተግባሩን  አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።

የመንግስት ሰራተኛው በየደረጃው የተቋቋመውን የሰላም ካውንስል እንቅስቃሴ ከመደገፍ ባሻገር በተሰማራበት የስራ መስክ ህብረተሰቡን በቅንነትና በታማኝነት ማገልገል እንደሚገባው አስገንዝበዋል ። 

በውይይት መድረኩ የከተማ አስተዳደሩ የተቋማት ሰራተኞችና በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም