በእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ከ4 ሺህ የሚልቁ የማህበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች በዛሬው ዕለት የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናን በመውስድ ላይ ናቸው

እንጅባራ፤ሐምሌ 3/2016(ኢዜአ)፦ በእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ከ4 ሺህ የሚልቁ የማህበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች በዛሬው ዕለት የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናን  እየወሰዱ መሆናቸውን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ጋርዳቸው ወርቁ አስታወቁ።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ጋርዳቸው ወርቁ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ዩኒቨርሲቲው ከአዊና እና መተከል ዞኖች የተውጣጡ 9 ሺህ 900 ተማሪዎችን በማህበራዊና የተፈጥሮ ሳይንስ ያስፈትናል።

በዩኒቨርሲቲው እንዲፈተኑ ከተመደቡት መካከል 4 ሺህ 200 የሚሆኑት የማህበራዊ ሳይንስ ተፈታኝ ተማሪዎች ከዛሬ ጀምሮ ፈተናውን መውሰድ መጀመራቸውን አስታውቀዋል።

ዩኒቨርሲቲው ፈተናውን በተሳካ ሁኔታ ለመስጠት የሚያስችለውን ተግባራት ሲያከናውን መቆየቱን አስታውሰው፣ በተደረገው ዝግጅት መሰረትም ፈተናው መሰጠት ጀምሯል ብለዋል።

በዛሬው ዕለትም ተፈታኞቹ የእንግሊዘኛና የሒሳብ የትምህርት ዓይነቶችን መፈተናቸውን ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል።

በቀጣይም ፈተናው በተጀመረው አግባብ እንዲጠናቀቅ የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሰራር ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አብራርተዋል።

ዩኒቨርሲቲው በሁለተኛው ዙር የሚሰጠውን የተፈጥሮ ሳይንስ ፈተና በተመሳሳይ ሁኔታ ለመስጠት በቂ ዝግጅት ማድረጉንም ዶክተር ጋርዳቸው አስታውቀዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም