ኢትዮ ቴሌኮም በዲጂታል ኢትዮጵያ ግንባታ ሂደት የመሪነት ሚናውን እየተወጣ ነው - ፍሬህይወት ታምሩ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 3/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮ ቴሌኮም አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ገቢራዊ በማድረግ ለዲጂታል ኢትዮጵያ ግንባታ የመሪነት ሚናውን እየተወጣ መሆኑን ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ ፍሬህይወት ታምሩ ገለጹ፡፡

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ የኩባንያውን የ2016 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም በተመለከተ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም በ2016 በጀት ዓመት ሁሉንም ማህበረሰብ የሚያሳትፍ፤ የሀገሪቷን ሁለንተናዊ ዕድገት የሚያረጋግጥና ዓለም አቀፋዊ ነባራዊ ሁኔታን ታሳቢ ያደረገ ዕቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ መገባቱን ገልጸዋል።

ከ2015 ጀምሮ ለሶስት ዓመታት በሚቆየው መሪ የዕድገት ስትራቴጂው የቴክኖሎጂ ልህቀትን ማረጋገጥ፣ ከፍተኛ አፈፃፀም ያለው ተቋም መገንባት፣ በአጋሮችና በደንበኞች ተመራጭ መሆን የትኩረት መስኮች መሆናቸውን አስታውሰዋል።

በዚህም የዲጂታል ኢትዮጵያን ግንባታ እውን ማድረግ የሚያስችሉ ውጤቶች መገኘታቸውንና ስራው ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።

ለአብነት የቴሌብር አገልግሎት ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን 2 ነጥብ 55 ትሪሊዬን ብር ግብይት መፈጸሙን አንስተዋል ፡፡

ቴሌብር ለዜጎች የሚሰጠውን አገልግሎት በማቀላጠፍ የዲጅታል ኢትዮጵያን ግንባታ እያገዘ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

አሁን ላይ የቴሌ ብር ተጠቃሚዎች ቁጥር 47 ነጥብ 5 ሚሊዬን መድረሱንና በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ብቻ 1 ነጥብ 8 ትሪሊዬን ብር ግብይት መከናወኑን ነው የገለጹት፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም የ2016 በጀት ዓመት እቅዱን በስኬት ማጠናቀቁን የገለጹት ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ፤  462 አዳዲስ የሞባይል ጣቢያዎች ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮ ቴሌኮም 86 ሚሊዮን ደንበኞችን ማስተናገድ የሚያስችል የሞባይል ኔትወርክ አቅም መገንባቱን በመጠቆም የ4G አገልግሎት 34 ነጥብ 6 በመቶ ደርሷል ብለዋል።


 

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በ124 ከተሞች የ4G አገልግሎት በመስጠት የ4G ተጠቃሚ ከተሞችን 424 ማድረስ መቻሉን ገልጸዋል።

ከዚህም ባለፈ 132 የገጠር የሞባይል ጣቢያዎች ከ2G ወደ 3G አገልግሎት ማደጋቸውን ጠቅሰው፤ በአምስት ከተሞች የ5G አገልግሎት ማስፋፊያ መደረጉንና በሂደት ላይ ያሉ መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ቀደም የሞባይል ኔትወርክ ያልነበራቸውን 216 የገጠር ቀበሌዎች በኔትወርክ ማስተሳሰር መቻሉን ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ አስታውቀዋል።

በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በተከሰቱ ግጭቶች የወደሙ የቴሌኮም መሰረተ ልማቶችን በመጠገን መልሶ ወደ ስራ ማስገባት መቻሉን ተናግረዋል ፡፡

በዚህም ጉዳት የደረሰባቸውን 179 የቴሌኮም ጣቢያዎች እና 570 ኪሎ ሜትር የፋይበር ጥገና በማከናወን ህብረተሰቡ ዳግም የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆን መደረጉን ገልጸዋል፡፡

በአጠቃላይ የሞባይል ኔትወርክ ተደራሽነት በቆዳ ስፋት 85 ነጥብ 4 ፤ በተጠቃሚዎች ደግሞ ከ99 በመቶ በላይ መድረሱን ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም የደንበኞችን ፍላጎት መሰረት ያደረጉ ምርትና አገልግሎቶችን ከማቅረብና ማህበራዊ ሃላፊነቱን ከመወጣት ባለፈ ለመንግስት ገቢ በማስገኘትም ሚናው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዚህም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 93 ነጥብ 7 ቢሊየን ገቢ በማግኘት የዕቅዱን 103 ነጥብ 6 በመቶ ማሳካት መቻሉን አስታውቀዋል፡፡

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም