በኢትዮጵያ ለኮቪድ-19 የተሰጠው ምላሽ ወረርሽኞችን ቀድሞ መከላከልና መቆጣጠር የሚያስችል አቅም እንዲገነባ አስችሏል

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 3/2016(ኢዜአ)፦  በኢትዮጵያ ለኮቪድ-19 የተሰጠው ምላሽ በአገሪቱ ሊከሰቱ የሚችሉ ወረርሽኞችን ቀድሞ መከላከልና መቆጣጠር የሚያስችል አቅምን በመገንባት ዝግጁነትን ለማዳበር ምቹ ሁኔታ መፍጠር  ችሏል።

ጤና ሚኒስቴር ፓዝ ከተሰኘ በጤና ላይ ከሚሰራ አለም አቀፍ ድርጅት ጋር በመተባበር የኮቪድ-19 ምላሽ አሰጣጥ በኢትዮጵያ ምን እንደሚመስል ያከናወነውን ጥናት ይፋ አድርጓል።

በመደበኛ የጤና አገልግሎት፣ በክትባት፣ በእናቶችና ህፃናት ጤና ላይ የሚሰራው የፓዝ ኢትዮጵያ የጥናት አስተባባሪ ዶክተር ሙሉነህ ይግዛው ባቀረቡት ጥናት ዓለም አቀፍ ተለዋዋጭ ሁኔታዎች ለወረርሽኝ መከሰትና መስፋፋት ምንጭ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ፣ የአለም ህዝብ ቁጥር መጨመርና የቴክኖሎጂ መስፋፋት ለወረርሽኝ መፈጠርና መዛመት ምክንያት መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

በተለይም በማደግ ላይ ባሉ አገራት የወረርሽኞች የመከሰት ዕድል ሰፊ በመሆኑ የተጋላጭነት ምጣኔውም በዚያው ልክ እንደሚጨምር ጠቅሰዋል። 

ጥናቱ በአለም አቀፍ ደረጃ ተከስቶ በነበረው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ላይ ትኩረቱን ያደረግ እንደሆነና በኢትዮጵያ ለወረርሽኙ የተሰጠው ምላሽና አመላካች ውጤቶች ምንድን ናቸው በሚል ማጠንጠኛ የተካሔደ መሆኑን ጠቁመዋል።

በጥናቱ 233 የጤና ድርጅቶች፣ 81ግለሰቦች፣ 952 የጤና ባለሙያዎችና አመራሮች መሳተፋቸውን በመጥቀስ በወቅቱ በኮቪድ-19 ዙሪያ የሚወጡ አገራዊ መረጃዎችን በመጠቀም የተካሄደ ስለመሆኑም አንስተዋል።

በአገሪቱ ወረርሽኞችን በተናበበ መልኩ ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችል አሰራር ባለመዘርጋቱ በወቅቱ ከፍተኛ ስጋት ፈጥሮ እንደነበር አስታውሰዋል።

ነገር ግን በአገር አቀፍ ደረጃ ኮቪድ-19ኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተደረገው ጥረት አበረታች መሆኑ በጥናቱ ተመላክቷል።

በተለይም መንግስት ለጉዳዩ የሰጠው ትኩረትና ቁርጠኝነት ወረርሽኙ በተጠበቀው ልክ ጉዳት ሳያደርስ መግታት እንዲቻል ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከቱን በጥናት ግኝታቸው አመላክተዋል።

መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ አካላትን በማስተባበር በተሰጠው ምላሽ አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ ቢቻልም አሁንም ዝግጁነትን ማጠናከር ላይ ተከታታይነት ያለው ስራ መስራት እንደሚገባ በጥናቱ ተጠቅሷል።

በጤና ሚኒስቴር የፕሮግራምና የጤና አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ከፍተኛ አማካሪ አቶ ለሊሳ አማኑኤል እንደገለጹት ኢትዮጵያ የጤናውን ዘርፍ ለማሳደግ በትኩረት እየሰራች ትገኛለች።

በዚህም ወረርሽኞችን በቅድመ መከላከል ስራ መግታትና ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች ደግሞ በቂ የህክምና አገልግሎት የሚሰጥበትን ምቹ ሁኔታ በመፍጠር መከላከል አንዱና ዋነኛው መሆኑን አስረድተዋል።

በተጨማሪም የእናቶችና ህፃናት ጤና አጠባበቅን በማሻሻልና የሚከሰተውን የሞት ምጣኔ በመቀነስ ረገድ እንደ አገር በተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤት መመዝገቡን አንስተዋል።

ኮቪድ-19ኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር መንግስት በቁርጠኝነት መስራቱን አስታውሰው በዚህም ወረርሽኙ የተፈራውን ያህል ጉዳት ሳያደርስ መግታት ተችሏል ነው ያሉት።

ይህ ጥናት በዘርፉ ያሉትን ተግዳሮቶች በመቅረፍ ዝግጁነትና ቅድመ መከላከል ላይ ያለውን አገራዊ አቅም ይበልጥ ለማጠናከር የሚያግዝ ነው ብለዋል።

የፓዝ ኢትዮጵያ ዳይሬክተር ትርሲት ግርሻው በበኩላቸው በኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ የሚከናወኑ  ተግባራት የዜጎችን የጤና ሁኔታ ለማሻሻል ምቹ ሁኔታ እየፈጠሩ ይገኛሉ። 

በተለይም ወረርሽኞችን ቀድሞ ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚወሰደው እርምጃ እንደ አገር የሚያስመሰግንና አርአያ የሚሆን ነው በለዋል።

በመሆኑም ፓዝ ኢትዮጰያ የጤናውን ዘርፍ ለመደገፍና ለማገዝ የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም