ለሠላም  መስፈን  የበኩላቸውን  አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ በወልዲያ ከተማ አስተዳደር የመንግስት ሠራተኞች ገለጹ

ወልዲያ፤ሐምሌ 3/2016(ኢዜአ)፡- ለሠላምና መልካም አስተዳደር መስፈን የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ የወልዲያ ከተማ አስተዳደር የመንግሰት ሠራተኞች ገለጹ። 

"ሠላም ለሁሉም፣ ሁሉም ለሠላም" በሚል መሪ ሃሳብ  የመንግስት ሠራተኞች የተሳተፉበት የሠላም ኮንፈረንስ በወልዲያ ከተማ ዛሬ ተካሄዷል።

በኮንፈረንሱ አገራዊ፣ ክልላዊና አካባቢያዊ ሁኔታን መሠረት ያደረገ የመወያያ ሃሳብ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል። 

ከተሳታፊ የመንግስት ሠራተኞች መካከል አቶ ብዙነህ አስፋው በሰጡት አስተያየት፤ በነበረው ችግር  ያለመረጋጋትና የኑሮ ውድነትን ማስከተሉን አውስተዋል። 

ችግሮች እንዲፈቱ የመንግስት ሰራተኛው ሚና የጎላ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለዚህም  ግንባር ቀደም  በመሆን የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል። 

ችግሮችን በውይይት ለመፍታት መንግስት ያቀረበው የሰላም አማራጭ ተገቢና በአግባቡ መፈፀም እንዳለበትም አመልክተዋል። 

ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዞ ህዝቡ የሚነሳቸውን የጉድለት ችግሮች  በአግባቡ ለመፍታት ከሠላም ተግባራት ባላነሰ ትኩረት ሰጥተን እንሠራለን ሲሉ ገልጸዋል።

ችግሩን  በመነጋገር  ለመፍታት የቀረበው  የሠላም ጥሪ   የሚደግፉት መሆኑን የተናገሩት ደግሞ   ወይዘሮ በላይነሽ ደሱ ናቸው። 

አለመረጋጋቶች ይዘውት በመጡት ተጽዕኖ የመንግሰት ሠራተኞው ተጎጂ መሆኑን  በመጥቀስ ለሠላም መስፈን የበኩላቸውን እንደሚወጡ አስታውቀዋል።


 

የወልዲያ ከተማ አስተዳደር  ከንቲባ የህዝብ ተሳትፎና አደረጃጀት አማካሪ አቶ ተስፋዬ ገብሬ ፤  ችግሩን ለመፍታት የሠላም አማራጮችን  መጠቀም ተገቢ መሆኑን ተናግረዋል።

መንግስት ችግሩን በሰለጠነ አግባብ በምክክርና በመነጋገር ለመፍታት በተደጋጋሚ የሰላም እጅን መዘርጋቱን ጠቅሰው፤ ይህ እንዲሳካ ማገዝ እንደሚገባ አመልክተዋል። 

ከችግር የምንወጣው ሠላምን ስናሰፍን በመሆኑ በተለይ የመንግስት ሠራተኛው ለሠላም መከበር ጉልህ ሚናውን ሊወጣ ይገባል ሲሉ ገልጸዋል።

በሠላም ኮንፈረንሱ የከተማ አስተዳደሩ አመራር አባላትና የተቋማት የመንግስት ሠራተኞች ተሳታፊ ሆነዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም