የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል መስተዳደር ምክር ቤት የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳለፈ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 3/2016(ኢዜአ)፦የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል መስተዳደር ምክር ቤት በተለያዩ አጀንዳዎች ዙሪያ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል።

ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደዉ 32ኛ መደበኛ ስብሰባ በክልሉ በግብርና ኢንቨስትመንት በተለይም ገበያ ተኮር በሆኑ የቡናና የቅባት እህሎች ምርት እንዲሁም ዘመናዊ የእንስሳት ሃብት ልማትና መኖ አቅርቦት ማሳለጥ የሚያስችሉ 25 የተለያዩ ፕሮጀክቶችን መርምሮ 23ቱ ወደ ሥራ እንዲገቡ ውሳኔ አሳልፏል።

በመቀጠል የፍትህ ሥርዓት ማሻሻያ አካል የሆነውን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት የባህል ፍርድ ቤቶችን ለማቋቋምና እውቅና ለመስጠት የወጣውን ረቂቅ አዋጅ መርምሮ ለክልሉ ምክር ቤት እንዲመራ ተሰማምቷል፡፡

በተመሳሳይም በመንግሥትና መንግሥታዊ ባልሆኑ አጋር ድርጅቶች የተገነቡ የመስኖና የውሃ መፋሰሻ መሠረት ልማቶችን ለተጠቃሚዎች ለማስተላለፍና ለማስተዳደር ፣ የግብርና ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ የሚያስችል የክልሉ የመስኖ ውሃ ተጠቃሚዎች ማህበራት ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቶ ለክልሉ ምክር እንዲመራ ወስኗል።

በመጨረሻም ምክር ቤቱ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት የ2017 በጀት ዓመት የክልሉ መንግሥት ረቂቅ በጀት አዋጅ ላይ ሰፊ ውይይት በማድረግ ለክልሉ ምክር ቤት እንዲመራ መወሰኑን ከክልል ኮሙኒኬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም