በኢትዮጵያ ግጭትን በምክክር  በዘላቂነት ለመፍታት በሚደረገው ጥረት የምክር ቤት አባላት ድርሻቸውን  የበለጠ እንዲያጠናክሩ  ተጠየቀ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 3/2016(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ ግጭትን በምክክር  በዘላቂነት ለመፍታት በሚደረገው ጥረት የምክር ቤት አባላት ድርሻቸውን  የበለጠ እንዲያጠናክሩ  በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) ጠየቁ።

የምክር ቤት አባላት ወደ ምርጫ ክልሎቻቸው በክረምቱ በሚሄዱበት   ወቅት  በተለይም  ለሰላምና ልማት ቅድሚያ ሰጥተው   መስራት እንደሚገባቸውም አንስተዋል። 

የየካቲት ወር የውክልና ስራ ጥያቄዎችን አስመልክቶ ከአስፈጻሚ ተቋማት ጋር በተደረገው ውይይት ወቅትም የግብርና፣ የጤና፣ የትምህርት እና የሥራና ክህሎት ሚኒስትሮችና ተጠሪ ተቋማት ኃላፊዎች ከሕዝብ ለቀረቡ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

 የግብርና፣ የጤና፣ የትምህርትና የሥራና ክህሎት ሚኒስትሮችና ተጠሪ ተቋማት ኃላፊዎች ከሕዝብ ለቀረቡ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በዚሁ መድረክ ላይ የተገኙት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር)፤ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ መንግሥት እያደረገ ያለውን ያላሰለሰ ጥረት አንስተዋል።

በመሆኑም ግጭትን በማስቆም በምክክር በዘላቂነት ለመፍታት በሚደረገው ጥረት የምክር ቤት አባላት የበለጠ የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

ከሀገራዊ ለውጡ በኋላ እየተከናወኑ ባሉ ዘርፈ-ብዙ የልማት ሥራዎች ተስፋ ሰጪ ውጤቶች እየተመዘገቡ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለስኬታማነቱ የሁሉም እገዛ ያስፈልጋል ብለዋል።


 

በዚህ ረገድ የሕዝቡ ትብብርና እገዛ ወሳኝ በመሆኑ የምክር ቤት አባላት በየምርጫ ክልሎቻቸው ማወያየትና ሰፊ ግንዛቤ መፍጠር እንዳለባቸውም አንስተዋል።

ለሀገሪቷ ዘላቂ ሰላም፣ ለሕግ የበላይነት፣ የኑሮ ውድነትና የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት የጋራ ጥረቱ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።

ኢትዮጵያ እርዳታ ጠባቂ እንዳትሆን በአረንጓዴ አሻራ፣ በሌማት ትሩፋትና በሌሎችም መስኮች የተጀመሩትን የልማት ሥራዎች ከዳር እናድርስ ሲሉም ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም