በዘንድሮ የምርት ዘመን 15 ነጥብ5 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ወደ ሀገር ውስጥ ገብቷል

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 3/2016 (ኢዜአ)፦ በዘንድሮ የምርት ዘመን 20 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ግዢ ተፈፅሞ 15 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ወደ ሀገር ውስጥ መግባቱን የግብርና ሚኒስትር ዶክተር ግርማ አመንቴ ገለፁ።

የግብርና ሚኒስትር ዶክተር ግርማ አመንቴ የምክር ቤት አባላት በመራጭ ተመራጭ ውይይት መድረክ ከህዝቡ ለሰበሰቧቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በዚህም በዘንድሮ የምርት ዘመን የ20 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ግዢ ተፈፅሞ እስካሁን ባለው ሂደት 15 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ወደ ሀገር ውስጥ መግባቱን አስታውቀዋል።

በየቀኑ 100 ሺህ ኩንታል ማዳበሪያ ወደ ሀገር ውስጥ እየገባ መሆኑን በመጠቆም አሁን ላይ 2 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ጅቡቲ ወደብ መድረሱን ነው የተናገሩት።

ከማዳበሪያ አቅርቦት ጋር ተያይዞ የሚያጋጥሙ ብልሹ አሰራሮችን ለመፍታት በቂ አቅርቦት እንዲኖርና የማዳበሪያ ግዢን በዲጂታል መፈፀም የሚያስችል ስራ መከናወኑን አንስተዋል።

ማዳበሪያው ከጅቡቲ ተነስቶ አርሶ አደሩ እጅ እስኪገባ ያለውን ሂደት በዲጂታል ስርዓት ለመምራት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

የተሻሻሉ ዝርያዎችን በማሰራጨት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተከናወነ ያለው የምርጥ ዘር ብዜት ስራ መሻሻል እየታየበት መሆኑን ተናግረዋል።

ለአብነት የስንዴ ዘር ብዜት በመስኖ ልማት ጭምር መከናወኑንና የበቆሎ ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሩ መሠራጨቱን ገልፀዋል።

87 ከመቶ የምግብ ፍላጎት የሚሸፍኑ አምስት ሰብሎች ተለይተው የዘር ብዜት ስራ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የዘር አቅርቦትና ተደራሽነትን ለመምራት የተቋቋመው ኮሚቴ የዘር አባዥ ድርጅቶችን የመሬት አቅርቦት ችግር መለየቱን አንስተው ምክር ቤቱ ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም