ቀጥታ፡

 ደም በመለገስ የማይተካ ህይወትን ማዳን ውድ የሰው ልጅ ስጦታ ነው

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 3/2016(ኢዜአ)፦ ደም በመለገስ የማይተካ ህይወትን ማዳን ውድ የሰው ልጅ ስጦታ ነው።

አቶ ሀይለአብ አለማየሁ ላለፉት 22 ዓመታት ያለማቋርጥ በየሶስት ወሩ በቋሚነት ደም ሲለግስ መቆየቱንና ዘንድሮም ለ68ኛ ጊዜ ደም መለገሱን በደስታ ስሜት ተሞልቶ ተናግሯል፡፡

ይህ ሰብአዊ ተግባር በቁስ እና በገንዘብ ሊገለጽ የማይችል ደስታ እንደሚሰጠውና የበጎ ፍቃድ ተግባሩ ሕይወቱ በደስታ የተሞላ እንዲሆን እንዳስቻለውም ይናገራል። 

ሀይለአብ ዛሬ በጉልምስና እድሜ ውስጥ ቢገኝም ያኔ ገና በለጋ የወጣትነት ዕድሜው የጀመረው የበጎ ፈቃድ ደም ልገሳ ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት ቀዳሚ በጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾች አንዱ አድርጎታል።


 

ሌላኛዉ ቋሚ ደም ለጋሽ አቶ ቢንያም ተሻለ  ከ1993 ዓ.ም ጀምሮ በዓመት አራት ጊዜ ደም እንደሚሰጥና ዘንድሮ ለ74ኛ ጊዜ ደም መለገሱን ገልጿል ፡፡

አቶ ቢኒያም ደም በመለገሱ ከፍተኛ የህሊና እርካታ ማግኘቱንና በሚለግሰው ደም የሚተርፈውን የወገን ህይወት ሲያስብ በፍጹም ደስታ እንደሚሞላ ጠቅሷል፡፡


 

ላለፉት 33 ዓመታት ከ 98 ጊዜ በላይ ደም የለገሱት አቶ ዳዊት ተስፋዬ በበኩላቸው ደም በመለገሳቸው የደረሰባቸው አንዳችም የጤና እክል አለመኖሩን ተናግረዋል፡፡

ደም ለጋሾቹ በቋሚነት ደም መለገስ ከፍተኛ የጤና ጠቀሜታ እንዳለው ከጤና ባለሙያዎች መገንዘባቸውን በማስረዳት ህብረተሰቡ በፈቃደኛነት ደም የመለገስ ባህሉን እንዲያሳድግ አሳስበዋል፡፡

ደም ለጋሾቹ በቋሚነት በሚሰጡት ደም የወገንን ህይወት መታደግ መቻላቸው የነፍስ እርካታ የሚሰጥ መሆኑን ገልጸው በዚሁ በጎ ተግባር እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል ፡፡


 

የኢትዮጵያ ደም እና ህብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር  አሸናፊ ታዘበው  (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በየቀኑ በመቶዎች የሚቆጠሩ ቅን ልቦና ያላቸው ደም ለጋሾች በሚሰጡት ደም በሺዎች የሚቆጠሩ ወገኖችን ህይወት መታደግ መቻሉን ገልጸዋል ፡፡

ማንኛውም ጤነኛ ሰው በዚህ በጎ ተግባር በመሳተፍ ውድ የሆነውን የሰው ሕይወት ለማዳን እንዲረባረብ ጠይቀዋል ፡፡


 

 የጤና ሚኒስትር ዶክተር  መቅደስ ዳባ በበኩላቸው፤ ዛሬ ጤነኛ የሆነ ሰው ነገ ደም ፈላጊ የሚሆንበት አጋጣሚ ሊፈጠር እንደሚችል አስታውሰው ሁሉም ሰው ደም በመለገስ የድርሻውን እንዲወጣ አሳስበዋል።

በኢትዮጵያ 80 በመቶ የሚሆነው የደም ክምችት የሚገኘው ከተማሪዎች መሆኑን የጠቀሰው አገልግሎቱ፣ ትምህርት ቤቶች በሚዘጉበት ጊዜ የክረምት በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ደም በማሰባሰብ ሂደት ትልቁን ሚና እንደሚጫወቱ አስታውቋል፡፡

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም