በመዲናዋ የገበያ ማዕከላትና በሚዘጋጁ ባዛሮች ምርቶችን በጥሩ አማራጭና በተመጣጣኝ ዋጋ እየገዛን ነው - ሸማቾች 

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 3/2016(ኢዜአ)፦ በመዲናዋ የገበያ ማዕከላትና በሚዘጋጁ ባዛሮች ምርቶችን በጥሩ አማራጭና በተመጣጣኝ ዋጋ እየገዙ መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው ሸማቾች ገለጹ።

ከተማ አስተዳደሩ የኑሮ ውድነት ጫናን ለማቃለልና በተለይም የግብርና እና የኢንዱስትሪ ውጤቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ በብዛትና በጥራት እንዲቀርብ እየሰራ መሆኑ ይታወቃል።

የእሁድ ገበያን በማስፋፋትና በመዲናዋ መውጫ በሮች የገበያ ማእከላትን በመገንባት ጭምር ምርቶች በቀጥታ ከአርሶ አደሩ እንዲቀርቡ እየተደረገ ነው።

በእነዚህ የገበያ ስፍራዎችና በባዛር በሚቀርቡ ምርቶች በጥሩ አማራጭና በተመጣጣኝ ዋጋ እየሸመቱ መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው ሸማቾች ገልጸዋል።

በአቃቂ ቃሊቲ የገበያ ማእከል ሲሸምቱ ያገኘናቸው ወይዘሮ አመለወርቅ በጎሰው፣ ፍቅርአዲስ ጌታቸው እና ወይዘሮ ወርቅውሃ ባዲ፤ በማእከላቱ በቀጥታ ከአምራቾቹ በተመጣጣኝ ዋጋ ጥራት ያለው ምረት እየገዛን ነው ብለዋል።

የማዕከላቱ ግብይት ከመደበኛ የገበያ ዋጋ አንፃር ሲታይ ከፍተኛ ልዩነት ያለው መሆኑን ጠቅሰው እንዲህ አይነት አማራጮች በመኖራቸው ተደስተናል ሲሉ ተናግረዋል።

ከተለያዩ አካባቢዎች በመምጣት በአቃቂ ቃሊቲ የግብርና ምርቶች የገበያ ማዕከል የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶችን ሲሸጡ ያገኘናቸው አምራቾች ገበያው ለሁላችንም ጠቀሜታ ያለው ነው ብለዋል።

ከደቡብ ኢትዮጵያ ባስኬቶ ዞን የመጡት አቶ አጌና አውስቶ እና አቶ  ዳንኤል ብርሀኑ፤ የደላላ ጣልቃ ገብነት ሳይኖር የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶችን በቀጥታ ለተጠቃሚው እያቀረቡ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም