የኦሮሚያ ክልል ከተሞች ህዝቡን የመልማት ጥያቄ መሰረት ያደረጉ መሰረተ ልማት እንዲኖራቸው ይሰራል - አፈ ጉባዔ ሰዓዳ አብዱረህማን - ኢዜአ አማርኛ
የኦሮሚያ ክልል ከተሞች ህዝቡን የመልማት ጥያቄ መሰረት ያደረጉ መሰረተ ልማት እንዲኖራቸው ይሰራል - አፈ ጉባዔ ሰዓዳ አብዱረህማን

አዳማ፤ ሐምሌ 3/2016(ኢዜአ)፡-የክልሉ ከተሞች የህዝቡን የመልማት ጥያቄ መሰረት ያደረጉና ደረጃቸውን የጠበቁ መሰረተ ልማት እንዲኖራቸው የክልሉ መንግሥት እየሰራ መሆኑን የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሰዓዳ አብዱረህማን ገለጹ።
በሞጆ ከተማ ከ360 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነቡ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ፕሮጀክቶች ዛሬ ለአገልግሎት ክፍት ሆነዋል።
የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሰዓዳ አብዱረህማን በዚሁ ወቅት የከተሞች ዕድገትና ውበት የሚረጋገጠው በመሰረተ ልማት ዝርጋታና በሚያመነጩት ገቢ በመሆኑ ሞጆም የጀመረችውን የልማት ስራዎች አጠናክራ መቀጠል አለባት።
ሞጆን የህዝብና የሎጀስቲክስ አገልግሎት የተረጋገጠባትና የኢንዱስትሪ ማዕከልነቷን በጠበቀ መልኩ የልማት ዝርጋታ አሁንም በልዩ ትኩረት እንዲሰራ አስገንዝበዋል።
አፈጉባዔዋ እንዳሉት የክልሉ ከተሞች የህዝቡን የመልማት ጥያቄ መሰረት ያደረጉና ደረጃቸውን የጠበቁ መሰረተ ልማት እንዲኖራቸው የክልሉ መንግስት በትኩረት እየሰራ ይገኛል።
በተለይም የዜግነት የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች ስራ የከተሞችን አቅመ ደካሞች ተጠቃሚ ያደረጉ ከመሆኑም ባለፈ፤ የአስተዳደሩ አቅም ያልደረሰበትን ክፍተት እየሞላ በመሆኑ በተያዘው ክረምት ተጠናክሮ እንዲቀጥልም አሳስበዋል።
የሞጆ ከተማ ከንቲባ አቶ ገዛሊ ሀሹ በበኩላቸው ሞጆ የሎጀስቲክ ማዕከል እንዲትሆን የሚያስችሉ መሰረተ ልማቶች እንዲኖሯት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይም የንግድና ኢንቨስትመንት ማዕከል ለማድረግ ደረጃቸውን የጠበቁ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ስራዎች በጥራት እየተከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በዚህም የህዝቡን የመልማት ጥያቄ የሚመልሱ የመንገድ፣ የውሃ፣ የአረንጓዴ ፓርክ፣ የአቅመ ደካማ ቤቶች፣ የዶሮና ወተት ላሞች እርባታ ማዕከላት በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው ብለዋል።
በተለይም 200 የአረጋዊያንና አቅመ ደካሞች ቤቶች ጥገናና እድሳት መከናወኑንም አንስተዋል።
የከተማዋን ገቢ ለማሳደግ በተደረገው ርብርብም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን ከንቲባው አስታውቀዋል።
በተጨማሪም ስምንት ኪሎ ሜትር የእግረኛና የኮብል ድንጋይ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች የተገነቡ ሲሆን፣ በዋና ዋና መስመሮች ላይም መብራት መዘርጋቱን አቶ ገዛሊ አመልክተዋል።
የከተማዋ ፅዳትና አረንጓዴነትን ለማረጋገጥ የደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ ተሽከርካሪዎችን በማስገባት አገልግሎት ማስጀመራቸውንም ገልጸዋል።
ከሞጆ ከተማ ነዋሪዎች መካከል አቶ መልካ ለሚ በከተማዋ የተገነባው አረንጓዴ ፓርክ ለነዋሪዎችና ወጣቶች የመዝናኛ ቦታ ሊሆን መብቃቱን ተናግረዋል።
ፓርኩ የተገነባበት ስፍራ ቀደም ሲል ቆሻሻ የሚጣልበትና የከተማዋን ውበት ያጎደፈ ነበር ያሉት ነዋሪው፣ በዘንድሮው ዓመት የከተማው አስተዳደር ያማረ መዝናኛ ቦታ ሰርቷል ብለዋል።
ከተማዋ የውሃ እጥረት የነበረባት በመሆኑ ውሃ በፈረቃ እንደሚያገኙ የተናገሩት አቶ መልካ፣ በአሁኑ ወቅት 24 ሳዓት የውሃ አገልግሎት ተጠቃሚ ለመሆን እንደቻሉ አስረድተዋል።
ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ ተስፋዬ ተሊላ በበኩላቸው በከተማዋ አገልግሎት ለማግኘት ረጅም ጉዞ ያደርጉበት የነበረውን ለማስቀረትና ጊዜና ጉልበት ለማዳን ያስቻሉ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት በቀበሌያቸው የአስተዳደር ህንፃ በመገንባቱ የተሻለ አገልግሎት ለማግኘት እንደሚያስችላቸውም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።