ለሰላም ካውንስሉ የሰላም ጥሪ መሳካት የበኩላቸውን እንደሚወጡ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን የመንግስት ሰራተኞች አስታወቁ

ጎንደር፤ ሐምሌ 3/2016(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የሰላም ካውንስሉ ያቀረበው የሰላም ጥሪ  እንዲሳካ በመደገፍ የድርሻቸውን እንደሚወጡ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን የመንግስት ሰራተኞች አስታወቁ። 

''ሰላም ለሁሉም ሁሉም ለሰላም'' በሚል መሪ ሃሳብ የዞኑ የመንግስት ሰራተኞች በጎንደር ከተማ የሰላም ኮንፍረንስ ዛሬ አካሂደዋል፡፡

የመንግስት ሰራተኞቹ በሰጡት አስተያየት፤ በክልሉ በነበረው ችግር ሰብአዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ማድረሱን ተናግረዋል፡፡

ከኮንፍረንሱ ተሳታፊ የመንግስት ሰራተኞች መካከል ወይዘሮ ገበያ ተገኘ እንዳሉት፤ የሰላም ካውንስሉ የሰላም ጥሪ ወቅታዊና ተገቢ ነው።

ይህም ለክልሉና ለዞኑ ዘላቂ ሰላም መረጋገጥ ፋይዳው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ሰላም በአንድ ወገን ጥረትና ፍላጎት ሊሳካ የማይችል በመሆኑ ችግሮችን ለመፍታት የሰላም ካውንስሉ ያቀረበውን ጥሪ በመቀበል ለውይይት ቅድሚያ ሊሰጡ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

የመንግስት ሰራተኛው ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት የሰላም ጥረቶች እንዲሳኩ የድርሻውን የመወጣት ግዴታም ሃላፊነትም አለበት ያሉት ደግሞ ሌላው ተሳታፊ አቶ አበባቸው ባዩ ናቸው፡፡

ሰላም ለሁሉም እንቅስቃሴ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፤ የሰላም ካውንስሉ ጥሪ የሰላም ጥረቶችን ለማሳካት ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር መሆኑንና ለዚህም መሳካት የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

ሌላው ተሳታፊ አቶ አበባው ዘውዱ፤ የሰላም ጥረቶች የሚሳኩት በሁሉም አካላት የተቀናጀ ጥረትና ርብርብ በመሆኑ ለሰላም ቅድሚያ እንደሚሰጡ ገልጸዋል፡፡

ልማትም ሆነ እድገት እውን ሊሆን የሚችለው ሰላም ሲረጋገጥ ብቻ እንደሆነ አመልክተው፤ የሰላም ካውንስሉ የሰላም ጥሪ ከልብ እንደሚደግፉና ለተግባራዊነቱም የበኩላቸውን እንደሚወጡ ጠቁመዋል፡፡

የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ወርቁ ሃይለማርያም፤ የመንግስት ቁርጠኛ የሰላም ጥረት ተሳክቶ በክልሉ ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ ሰራተኛው የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አመልክተዋል።

የሰላም ካውንስሉ ላቀረበው የሰላም ጥሪ መሳካት መንግስት ቁርጠኛ አቋም እንዳለው ገልጸዋል።

በሰላም ኮንፍረንሱ የተለያዩ ሴክተር መስሪያ ቤቶች ሰራተኞችና የስራ ሃላፊዎች ተሳታፊ ሆነዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም