ቀጥታ፡

ሀገር አቀፍ የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ፈተና እየተሰጠ ነው

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 3/2016(ኢዜአ)፦የ2016 የትምህርት ዘመን ሀገር አቀፍ የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ፈተና እየተሰጠ ነው፡፡

የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አራት ኪሎ ካምፓስ በመገኘት ፈተናውን አስጀምረዋል።

የማኅበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች ከሐምሌ 3 እስከ 5 ቀን 2016 ዓ.ም የሚወስዱ በመሆኑ በዚህም መሰረት በዛሬው እለት ፈተናው ተጀምሯል።

የኢዜአ ሪፖርተሮችም አራት ኪሎ ካምባስ እና በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በመገኘት የፈተናውን አሰጣጥ በተመለከተ ቅኝት አድርገዋል።

ፈተናው የተማሪዎችን ፍላጎት መሰረት በማድረግ በኦን ላይንና በወረቀት የተዘጋጀ በመሆኑ በዚሁ መሰረት ተማሪዎች በመፈተን ላይ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ፍቅሬ ደሳለኝ፤ ለፈተናው ዝግጅት ተደርጎና ለተማሪዎችም ገለፃ ተደርጎ በተረጋጋ ሁኔታ በመሰጠት ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

 

በዚህም መሰረት በዩኒቨርሲቲው 3 ሺህ 388 ተማሪዎች የመልቀቂያ ፈተናቸውን መውሰድ ላይ ይገኛሉ ብለዋል።

ለፈተናው ከ200 በላይ ሱፐርቫይዘሮች፣ ፈታኝ መምህራንና የጣቢያ ሃላፊዎች የተመደቡ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በበየነ-መረብ ለሚፈተኑ ተማሪዎችም በሂደቱ እንዳይቸገሩ በቂ ዘግጅት ተደርጓል ብለዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ ዘንድሮ 701 ሺህ 489 ተማሪዎች የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ የማጠናቀቂያ ፈተና የሚወስዱ መሆኑን የትምህርት ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም