ምክር ቤቱ  የህዝቡ የልማት ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ በአስፈጻሚ ተቋማት ላይ የሚያደርገውን ቁጥጥር አጠናክሮ ይቀጥላል-ምክትል አፈ-ጉባኤ ሎሚ በዶ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 3/2016(ኢዜአ)፦ህዝብ በየጊዜው ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች ተቋማት ተገቢ ምላሽ እንዲሰጡ የማድረግና ተጠያቂነትን የማስፈን ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ሎሚ በዶ ገለፁ።

በምክር ቤቱ የአሰራርና አባላት ስነ-ምግባር ደንብ መሰረት የምክር ቤቱ አባላት በዓመት ሁለት ጊዜ ወደ ምርጫ ጣቢያቸው ሄደው ህዝባዊ ውይይት ያካሂዳሉ።

በዚህ መሰረት በተያዘው በጀት ዓመትም የምክር ቤት አባላት በአብዛኛዎቹ የምርጫ ክልሎች ተገኝተው ህዝባዊ ውይይቶችን አድርገዋል።

በዚህም ከ284 ሺህ በላይ ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በውይይቱ በመሳተፍ የተለያዩ ጥያቄዎችን አንስተዋል።

በህዝባዊ መድረኮች በተነሱ ጥያቄዎች ዙሪያም የሚመለከታቸው መስሪያ ቤቶችና ተጠሪ ተቋማት ከምክር ቤቱ አመራርና አባላት ጋር ውይይት እያደረጉ ነው።

ምክትል አፈ-ጉባኤ ሎሚ በዶ እንዳሉት 6ኛው ዙር የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ3ኛ ዓመት የስራ ዘመኑ ከ15 በላይ ተቋማትን የስራ አፈፃፀም ተገምግሟል። 

ተቋማቱ ከመራጩ ህዝብ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ መስጠታቸውንም ተናግረዋል።

ከመራጩ ህዝብ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ እየሰጡ ከሚገኙ ተቋማት መካከል የትምህርት፣ የግብርና፣ የጤና፣ ስራና ክህሎት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችና ሌሎች ተጠሪ ተቋማት ይገኙበታል ነው ያሉት።

ምክር ቤቱ የህዝብ ውክልና ስራውን በአግባቡ ለመወጣት በየዘርፉ የተነሱ ጥያቄዎችን በማደራጀት ለሚመለከታቸው ተቋማት ማሳወቁንና ፈጣን ምላሽ እንዲሰጡ ክትትል እያደረገ መሆኑን ገልፀዋል።

እንዲህ አይነት አሰራር የህዝብ ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ እን ዲያገኝ የሚያስችል ነው ብለዋል።

ለህዝብ ጥያቄ ምላሽ የማይሰጡ ተቋማትን ተጠያቂ ለማድረግ ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው በማንሳት ተጠያቂነትን የማስፈን ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።

ምክር ቤቱ በ2016 በጀት ዓመት ከ59 በላይ የተለያዩ ረቂቅ አዋጆች ከሚኒስትሮች ምክር ቤት የተላከለት መሆኑንም ነው የተናገሩት።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም