በኢትዮጵያ የ4G አገልግሎት ተጠቃሚ ከተሞች 424 ደርሰዋል

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 3/2016(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ የ4G አገልግሎት ተጠቃሚ ከተሞች 424 መድረሳቸውን የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ ገለጹ።

ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ የኩባንያውን የ2016 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም በተመለከተ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም በ2016 በጀት ዓመት ሁሉንም ማህበረሰብ የሚያሳትፍ፤ የሀገሪቷን ሁለንተናዊ ዕድገት የሚያረጋግጥና ዓለም አቀፋዊ ነባራዊ ሁኔታን ታሳቢ ያደረገ ዕቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ መገባቱን ገልጸዋል።

ከ2015 ጀምሮ ለሶስት ዓመታት በሚቆየው መሪ የዕድገት ስትራቴጂው የቴክኖሎጂ ልህቀትን ማረጋገጥ፣ ከፍተኛ አፈፃፀም ያለው ተቋም መገንባት፣ በአጋሮችና በደንበኞች ተመራጭ መሆን የትኩረት መስኮች መሆናቸውን አስታውሰዋል።

በዚህም የዲጂታል ኢትዮጵያን ግንባታ እውን ማድረግ የሚያስችሉ ውጤቶች መገኘታቸውን ጠቅሰው ስራው ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።

በ2016 በጀት ዓመትም 462 አዳዲስ የሞባይል ጣቢያዎች ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ተናግረዋል።

ከዚህም ባለፈ 132 የገጠር የሞባይል ጣቢያዎች ከ2G ወደ 3G አገልግሎት ማደጋቸውን ገልጸዋል።

ኢትዮ ቴሌኮም 86 ሚሊዮን ደንበኞችን ማስተናገድ የሚያስችል የሞባይል ኔትወርክ አቅም መገንባቱን ገልጸው፣ የ4G አገልግሎት 34 ነጥብ 6 በመቶ ደርሷል ብለዋል።

በተጠናቀቀው በጀት በ124 ከተሞች የ4G አገልግሎት በመስጠት የ4G ተጠቃሚ ከተሞችን ወደ 424 ማድረስ መቻሉን ገልጸዋል።

በአምስት ከተሞች የ5G አገልግሎት ማስፋፊያ መደረጉን ጠቅሰው ሌሎች በሂደት ላይ ያሉ መኖራቸውንም ጠቁመዋል።

ከዚህ ቀደም የሞባይል ኔትወርክ ያልነበራቸውን 216 የገጠር ቀበሌዎች በኔትወርክ ማስተሳሰር ተችሏል ብለዋል።

የሞባይል ኔትወርክ ተደራሽነት በቆዳ ስፋት 85 ነጥብ 4፤ በተጠቃሚዎች ደግሞ ከ99 በመቶ በላይ ደርሷል ብለዋል።

የዲጂታል ኢትዮጵያን እቅድ ዕውን ለማድረግ እየተደረገ ያለው ጥረት በጥሩ ሂደት ላይ መሆኑን ጠቅሰው የ93 ነጥብ 7 ቢሊየን ገቢ የተገኘበት መሆኑንም አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም