የአማራ ክልልን  ሠላም በዘላቂነት ለማስጠበቅ  የመንግስት ሠራተኛው የድርሻውን መወጣት እንዳለበት ተመለከተ

ደብረ ብርሃን፤  ሐምሌ 3 ቀን 2016(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል ችግሮችን በውይይት በመፍታት  ሠላም በዘላቂነት  ለማስጠበቅ   የመንግስት ሠራተኛው የድርሻውን መወጣት እንዳለበት ተመለከተ። 

የደብረብርሃን ከተማ አስተዳደር የመንግስት ሠራተኞች የተሳተፉበት  የሠላም ኮንፍረንስ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

ኮንፍረንሱ እየተካሄደ ያለው  "ሠላም ለሁሉም ሁሉም ለሠላም" በሚል መሪ ሃሳብ ነው። 

የደብረ ብርሀን ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ  አቶ በድሉ ውብሸት እንደገለጹት፤ ባለፉት ወራት የአካባቢውን ብሎም የክልሉ ሠላም ለማስጠበቅ በተደረገው ጥረት ውስጥ የመንግስት ሰራተኛው ሚና የላቀ ነው።

በከተማው ሠላምን ከማፅናት ጎን ለጎን  የልማት ሥራዎች አጠናክሮ የማስቀጠል እንቅስቃሴ ስራ በቅንጅት እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ሠላሙን በህብረተሰቡ የነቃ ተሳትፎ ዘላቂ ለማድረግ በየደረጃው ከሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት ሲካሄድ መቆየቱንም አንስተዋል።

በክልሉ  ችግሮችን በውይይት በመፍታት  ሠላም በዘላቂነት  ለማስጠበቅ   የመንግስት ሠራተኛው ድጋፉን በማጠናከር የድርሻውን መወጣት እንዳለበት አመልክተዋል።

በኮንፍረንሱ ላይ የመወያያ ሰነዱን ያቀረቡት  አቶ ተክለዮሐንስ ሀይለጊዮርጊስ በበኩላቸው፤ ሠላም እንዲረጋገጥ የመንግስት ሠራተኛው ተባብሮ መስራት እንዳለበት ተናግረዋል።

በተለይም የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ በሚደረጉ ስራዎች ሁሉ የመንግስት ሰራተኛው የነቃ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚጠበቅበት  ገልጸዋል።

በክልሉ ችግሮችን   በውይይትና ንግግር ለመፍታት መንግስት ቁርጠኛ አቋም ይዞ እየሰራ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ ለተቋቋመው የሠላም ካውንስል ውጤታማነት ሁሉም መደገፍ እንዳለበት አመልክተዋል።

በኮንፈረንሱ የከተማ አስተዳደሩ  የመንግስት ሠራተኞችና በየደረጀው የሚገኙ የአመራር አባላት በመሳተፍ ላይ  ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም