መንግስት ከህብረተሰቡ የሚነሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ምላሽ ለመስጠት በትኩረት ይሰራል-ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
መንግስት ከህብረተሰቡ የሚነሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ምላሽ ለመስጠት በትኩረት ይሰራል-ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 3/2016(ኢዜአ)፦ መንግስት ከህብረተሰቡ የሚነሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ምላሽ ለመስጠት በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) ገለጹ ፡፡
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በየካቲት ወር 2016 ዓ/ም በየምርጫ ክልላቸው ከመራጩ ህዝብ ጋር ውይይት ባደረጉበት ወቅት የተነሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለሚመለከታቸው የአስፈፃሚ ተቋማት ተደራሽ እንዲሆን ተደርጓል፡፡
በምክር ቤቱ ተደራጅተው ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የተላኩ ከህብረተሰቡ የተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ያገኙትንና ያላገኙትን በመለየት በቀጣይ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት የህብረተሰቡን የመልማት ጥያቄ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት እንዲቻል ከአስፈፃሚ ተቋማት ጋር ውይይት እያደረገ ይገኛል፡፡
ከህብረተሰቡ የተነሱትን ጥያቄዎች የመንግሥት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ወ/ሮ መሠረት ሀይሌ አቅርበዋል።
በውይይቱ የትምህርት፣ የጤና፣ የግብርና ሚኒስቴር፣ የስራና ክህሎት፣ የመብራት ኃይል እና የመብራት አገልግሎት እንዲሁም የአደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን የሥራ ኃላፊዎች ከህብረተሰቡ የተነሱ ጥያቄዎችን አስመልክቶ ምላሽና ማብራሪያ እየሰጡ ነው፡፡
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) በወቅቱ መንግስት ከህብረተሰቡ የሚነሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ምላሽ ለመስጠት በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ መናገራቸውን ከህዝብ ተወካየች ምክር ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።