ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና እየተሰጠ ነው 

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 3/2016(ኢዜአ)፦ በመዲናዋ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከሚሰጥባቸው የትምህርት ተቋማት አንዱ በሆነው የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ  ፈተናው እየተሰጠ መሆኑ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ፍቅሬ ደሳለኝ፤ ፈተናው ለተማሪዎች አስፈላጊው ገለፃ ከተደረገ በኋላ መሰጠት መጀመሩን አስታውቀዋል።

በዩኒቨርሲቲው ፈተናቸውን የሚወስዱ 3 ሺህ 388 ተማሪዎችን በመቀበል ለፈተናው የሚያስፈልጉና ተገቢ የሆነ መስተንግዶ እየተደረገላቸው እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በዛሬው ዕለትም የ2016 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ የማህበራዊ ሳይንስ የመጀመሪያው ዙር ተማሪዎች ፈተናቸውን በጥሩ ሁኔታ እየወሰዱ ነው ብለዋል።

በዩኒቨርሲቲው መሰጠት የተጀመረውን የመልቀቂያ ፈተና በሰላም ለማጠናቀቅ ከፈታኝ መምህራን እና ከዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ጋር አስፈላጊው ዝግጅት መከናወኑን ተናግረዋል።

ተፈታኞች በፈተና ወቅት የሚጠበቅባቸውን ግዴታ እና መብት እንዲሁም በዩኒቨርሲቲው በፈተና ቆይታቸው ሊፈጽሟቸው የሚገቡ ህገ-ደንቦች  በአግባቡ እያከበሩ መሆኑን ገልጸዋል።

የአንደኛ ዙር ተፈታኞች ከዛሬ ጀምሮ ለሚቀጥሉት 3 ተከታታይ ቀናት ፈተናቸውን እንደሚወስዱ ጠቁመዋል።

ከ200 በላይ ሱፐርቫይዘሮች፣ ፈታኝ መምህራን እና የጣቢያ ሀላፊዎች ወደ ዩኒቨርሲቲው ገብተው የፈተናውን መርሃ ግብር በተሳካ መልኩ መስጠታቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም