ኢትዮጵያ ከተለያዩ አገራት ለመጡ ከ1 ነጥብ 1 ሚሊዮን በላይ ስደተኞች ከለላና ድጋፍ እያደረገች ነው

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 3/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ አሁን ላይ ከተለያዩ አገራት ለመጡ ከ1 ነጥብ 1 ሚሊዮን በላይ ስደተኞች ከለላና ድጋፍ እያደረገች ቢሆንም ዓለም አቀፉ ማህብረሰብ በቂ ድጋፍ እያደረገ አለመሆኑን የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ዋና ዳይሬከተር ጠይባ ሀሰን ገለጹ።

ኢትዮጵያ የስደተኞች መነሻ፣ መተላለፊያና መዳረሻ ሀገር መሆኗን የብሔራዊ ፍልሰት ምክር ቤት መረጃ ያሳያል።

በርካታ ዜጎቿ በተለያየ ምክንያት በህገ ወጥ መንገድ ለስደት እየተዳረጉ በመዳረሻ ሀገራት ስቃይና እንግልት እየደረሰባቸው መሆኑም በተደጋጋሚ ይነሳል።

ለዚህም መንግስት መደበኛ ያልሆነ ስደትን ለመከላከልና በችግር ላይ የሚገኙ ዜጎችንም ከአገራት ጋር በመነጋገር ወደ ሀገራቸው ለመመለስ እየሰራ ይገኛል።

የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ዋና ዳይሬከተር ጠይባ ሀሰን፤ መደበኛ ያልሆነ የዜጎች ስደት ለሀገር ትልቅ ጫና የፈጠረ መሆኑን ይናገራሉ።

ኢትዮጵያ ከተለያዩ አገራት የሚመጡ ስደተኞችን እያስተናገደች ቢሆንም ዜጎቿ ደግሞ በህገ ወጥ ስደት ለችግር እየተዳረጉ በመሆኑ ጉዳዩ አሳሳቢ ሆኗል ብለዋል።

ከተለያዩ አገራት መንግስታት ጋር ዲፕሎማሲያዊ ውይይት በማድረግ መንግስት ዜጎችን ወደ ሀገር ቤት እየመለሰ መሆኑን ገልጸዋል።

ለአብነትም በሳዑዲ አረቢያ እስር ቤት በችግር ውስጥ የነበሩ ዜጎችን የመመለስ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ አሁን ላይ ከ26 አገራት የገቡ ከ1 ነጥብ 1  ሚሊዮን በላይ ፍልሰተኞችን ተቀብላ ተገቢውን ጥበቃና ከለላ በማድረግ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን በአግባቡ እየፈጸመች ትገኛለች ብለዋል።

በተለያዩ የዓለም አካባቢዎች ያሉ ግጭቶች፣ ድህነትና ስራ አጥነት ህገ ወጥ ስደትን እያባባሱ መሆኑን ጠቅሰው ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ፍልሰተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ መምጣቱንም ገልጸዋል።

ለችግሩ ምላሽ ለመስጠት ዓለም አቀፋዊ ትብብር ያስፈልጋል ያሉት ዋና ዳይሬከተሯ አሁን በተጨባጭ ያለው ትብብርና ድጋፍ ግን እየቀነሰ መሆኑን ተናግረዋል።

ለጋሽ ሀገራትም ጦርነትና መሰል ተደራራቢ ችግሮች ሳቢያ ለሰብዓዊ ድጋፍ የሚውል በቂ ሀብት ለመመደብ መቸገራቸውን እየገለጹ ነው ብለዋል።

በዚህም ምክንያት በኢትዮጵያ  ለስደተኞች ድጋፍ ከለጋሾች የሚገኘው ሀብት ውስን በመሆኑ ለችግሩ ምላሽ ለመስጠት ዓለም አቀፋዊ ትብብር እንድደረግ ጠይቀዋል።

ኢትዮጵያ ዓለም አቀፋዊ ለጋሾች የሚያደርጉት ድጋፍ እንዲጠናከር ከመጠየቅ ባለፈ ስደተኞችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ዘላቂ የፖሊሲ ስራዎችን እያከናወነች ነው ብለዋል።

በዚህም ስደተኞችንና ተቀባይ ማህበረሰቡን ያማከለ ዘላቂ የልማት ስራ እየተተገበረ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም