በከተማ አስተዳደሩ ከ5 ሺህ በላይ የፍትሐ ብሔር መዝገቦች ክርክር በማሸነፍ  ከ5 ቢሊዮን ብር በላይ ማዳን ተችሏል

 

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 3/2016(ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ2016 ዓ.ም በጀት ዓመት 5 ሺህ 44 የፍትሐ ብሔር መዝገቦች ክርክር በማሸነፍ ከ5 ቢሊዮን ብር በላይ ማዳን መቻሉን የከተማ አስተዳደሩ የፍትሕ ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ምክትል እና የክርክር ዘርፍ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ደጀኔ ለኢዜአ እንደገለጹት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በፍትሐ ብሔር ዘርፍ 8 ሺህ 514 መዝገቦች ለክርክር ቀርበው 5 ሺህ 352 ውሳኔ ተሰጥቶባቸዋል።

ከዚህም ውስጥ 5 ሺህ 44 መዝገቦች ለመንግስት የተወሰኑ ሲሆን በ308 መዝገቦች በመንግስት ላይ የተወሰነ  መሆኑን ጠቅሰዋል።

በመንግስት ላይ ውሳኔ ከተላለፈባቸው መዝገቦች መካከል በ113 መስማማቱንና ባልተስማማባቸው 195 መዝገቦች ላይ ደግሞ ይግባኝ መጠየቁን አመልክተዋል።

ለመንግስት በተወሰነባቸው መዝገቦች አማካኝነት ከ5 ነጥብ  2 ቢሊዮን ብር በላይ ማዳን መቻሉን ነው አቶ ተስፋዬ የጠቆሙት።  

ከመዝገቦቹ መካከል 3 ሺህ 162 መዝገቦች ደግሞ ወደ 2017 በጀት አመት መተላለፋቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ይህም ከ2015 በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር 1 ሺህ 870 መዘገቦችን በመቀነስ መሻሻል መታየቱን አንስተዋል። 

ሕገ ወጥ የመሬት ወረራ፣የመንግስት ቤቶችንና እየተተገበሩ የሚገኙ ፕሮጀክቶችን አስመልክቶ የሚደረጉ ክርክሮችና የግለሰብ አቤቱታዎች መዝገቦቹ በዋነኛነት ያተኮሩባቸው መሆናቸውን በመጠቆም።

በተያያዘም በበጀት ዓመቱ በፍትሐ ብሔር ጉዳይ በመንግስት ተቋማት መካከል የሚነሱ አለመግባባቶችን በድርድር ለመጨረስ 36 ጉዳዮች ቀርበው 34ቱ ተጠናቀው ቀሪዎቹ በሂደት ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

በፍትሐ ብሔር ጉዳዮች በፍርድ ቤት የመርታት አቅም በበጀት ዓመቱ ወደ 94 ነጥብ 25 በመቶ ከፍ ማለቱንና ይህም ተቋማዊ የማስፈጸም አቅምን ለማሻሻል በተከናወኑ ስራዎች የተገኘ ውጤት መሆኑን አስታውቀዋል።

በሌላ በኩል ከወንጀል ጉዳዮች ጋር በተገናኘ በበጀት ዓመቱ 12 ሺህ 847 መዝገቦች ቀርበው ሙሉ ለሙሉ ውሳኔ እንደተሰጠባቸው አመልክተዋል።

ከመዝገቦቹ መካከል 8 ሺህ 19 ጉዳዮች በዜጎች መካከል ዘላቂ ሰላምና መቀራረብ ለመፍጠር በማሰብ  በእርቅ እንዲያልቁ መደረጉን ጠቁመዋል።

በ2016 በጀት ዓመት የተገኙ መልካም አፈጻጸሞችን በማጠናከር በአዲሱ በጀት ዓመት ወደ ፍርድ ቤት የሚሄዱ ጉዳዮችን የመቀነስ ጉዳይ የተለየ ትኩረት እንደተሰጠው ተናግረዋል።

ለዚህም በአገልግሎት አሰጣጥና መልካም አስተዳደር ላይ የሚነሱ ቅሬታዎች ፈጣን ምላሽ እንዲያገኙ የመንግስት ተቋማት ሕግን ተከትለው እንዲሰሩ አስፈላጊውን የሕግ ድጋፍ የማድረግ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

ቢሮው ክርክር የሚያደርግባቸው መስኮች በማስፋት የመንግስትና ሕዝብ ጥቅምን ለማስጠበቅ በትኩረት ይሰራል ነው ያሉት አቶ ተስፋዬ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍትሕ ቢሮ በተሻሻለው የከተማው የአስፈጻሚ አካላት አዋጅ 84/2016 ከተሰጠው ስልጣንና ተግባራት መካከል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሕጋዊ ወኪል በመሆን የመዳኘት ስልጣን ባላቸው ማንኛውም ተቋማት ፊት ክስ እንደሚያቀርብ፣ መልስ እንደሚሰጥና ክርክር እንደሚያደርግ ያስቀምጣል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም