እንግሊዝና ኔዘርላንድስ በአውሮፓ ዋንጫው የፍጻሜ ተፋላሚ ለመሆን የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 3/2016(ኢዜአ)፦ በ17ኛው የአውሮፓ ዋንጫ የግማሽ ፍጻሜ ሁለተኛ መርሐ ግብር እንግሊዝ ከኔዘርላንድስ ዛሬ የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል።

ስፔን ለፍጻሜ የደረሰች የመጀመሪያ አገር ሆናለች።

እንግሊዝና ኔዘርላንድስ ከምሽቱ 4 ሰዓት 81 ሺህ 365 ተመልካች በሚያስተናግደው ሲግናል ኢዱና ፓርክ ስታዲየም ይጫወታሉ።

በሩብ ፍጻሜው እንግሊዝ ስዊዘርላንድን፣ ኔዘርላንድስ ተርኪዬን በማሸነፍ ግማሽ ፍጻሜውን ተቀላቅለዋል።

ሁለቱ ሀገራት በአውሮፓ ዋንጫ መድረክ ሲገናኙ የአሁኑ ለሶስተኛ ጊዜ ነው።

ጀርመን (በወቅቱ አጠራሯ ምዕራብ ጀርመን) እ.አ.አ በ1988 ባዘጋጀችው 8ኛው የአውሮፓ ዋንጫ በምድብ 2 ተገናኝተው ኔዘርላንዳዊው ኮከብ ማርኮ ቫንባስተን ሶስት ግቦችን አስቆጥሮ ሀትሪክ በመስራት አገሩ 3 ለ 1 እንድታሸንፍ አድርጓል።

ብራያን ሮብሰን ለእንግሊዝ በወቅቱ ብቸኛዋን ግብ ያስቆጠረ ተጫዋች ነው።

ኔዘርላንድስ በውድድሩ ለፍጻሜ ደርሳ ሩሲያን ( በቀድሞ ስያሜዋ ሶቪየት ሕብረት) 2 ለ 0 በማሸነፍ ዋንጫውን አንስታለች።

ብርቱካናማዎቹ በወቅቱ ዋንጫውን ሲያነሱ የቡድኑ ስብስብ ከነበሩ ተጫዋቾች መካከል የአሁኑ የኔዘርላንድስ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሮናልድ ኮማን ይገኙበታል።

እንግሊዝ እ.አ.አ በ1996 ባዘጋጀችው 10ኛው የአውሮፓ ዋንጫ በምድብ 1 የነበሩት ሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች ባደረጉት ጨዋታ አዘጋጇ ሀገር ቴዲ ሼሪንግሃምና አለን ሺረር በተመሳሳይ  ባስቆጠራቸው ሁለት ግቦች 4 ለ 1 አሸንፋለች።

ፓትሪክ ክላይቨርት ለኔዘርላንድስ ብቸኛዋን ግብ ከመረብ ያዋሃደ ተጫዋች ነው።

ሁለቱ ሀገራት ከዚህ ቀደም ባደረጓቸው 22 የእርስ በእርስ ጨዋታዎች ኔዘርላንድስ 7 ጊዜ በማሸነፍ መጠነኛ ብልጫ ወስዳለች፤ እንግሊዝ 6 ጊዜ ስታሸንፍ 9 ጊዜ አቻ ተለያይተዋል።

ሀገራቱ ለመጨረሻ ጊዜ የተገናኙት እ.አ.አ በ2019 በዩኤፋ ኔሽንስ ሊግ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ላይ ነበር። በጨዋታው ኔዘርላንድስ 3 ለ 1 በማሸነፍ ለፍጻሜ አልፋለች።

እንግሊዝ በ17ኛው የአውሮፓ ዋንጫ እስከ አሁን ባደረገቻቸው 5 ጨዋታዎች 5 ጎሎችን ስታስቆጥር 3 ግቦችን አስተናግዳለች።

ኔዘርላንድስ በ5ቱ ጨዋታዎች 9 ግቦችን ከመረብ ላይ ስታሳርፍ 5 ግቦች ተቆጥሮባታል። 

ከእንግሊዝ የ21 ዓመቱ አማካይ ጁድ ቤሊንግሃም፣ 3 ጎሎችን በማስቆጠር የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ለመሆን እየተፎካከረ የሚገኘው የ25 ዓመቱ የኔዘርላንድ የክንፍ መስመር ተሰላፊ ኮዲ ጋፕኮ በጨዋታው የሚጠበቁ ተጫዋቾች ናቸው።

በፊፋ የሀገራት የእግር ኳስ ደረጃ እንግሊዝ 5ኛ እንዲሁም ኔዘርላንድ 7ኛ ላይ ተቀምጠዋል።

የ43 ዓመቱ ጀርመናዊ ፍሊክስ ዝዋየር ተጠባቂውን ጨዋታ በዋና ዳኝነት ይመሩታል።

የግማሽ ፍጻሜው ጨዋታ አሸናፊ  በፍጻሜው ከስፔን ጋር ይጫወታል።

ትናንት በተደረገው የመጀመሪያው የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ስፔን ፈረንሳይን 2 ለ 1 በማሸነፍ ለፍጻሜ ማለፏ ይታወቃል። 

 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም