ላሚን ያማል በአውሮፓ ዋንጫው አዲስ ታሪክ ሰራ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 2/2016(ኢዜአ)፦ስፔናዊው ታዳጊ ላሚን ያማል በአውሮፓ ዋንጫ ታሪክ ግብ ያስቆጠረ በእድሜ ትንሹ ተጫዋች ሆኗል።

በ17ኛው የአውሮፓ ዋንጫ የመጀመሪያ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ በስፔንና ፈረንሳይ መካከል በአሊያንዝ አሬና ስታዲየም በመካሄድ ላይ ይገኛል።

በጨዋታው ስፔናዊው ታዳጊ ኮከብ ላሚን ያማል ከፍጹም ቅጣት ክልል ውጪ ድንቅ ግብ አስቆጥሯል።

ይህን ተከትሎም ያማል በ16 ዓመት ከ362 ቀናት እድሜው ኳስን ከመረብ ጋር በማገናኘት በውድድሩ ታሪክ ግብ ያስቆጠረ በእድሜ ትንሹ ተጫዋች ክብረ ወሰንን ሰብሯል።

ከዚህ ቀደም ይህ ክብረ ወሰን ተይዞ የነበረው በስዊዘርላንዳዊው ጆሃን ቮላንተን ሲሆን ግብ ሲያስቆጥር እድሜው 18 ዓመት ከ141 ቀናት ነበር።

ያማል በዘንድሮው የአውሮፓ ዋንጫ ስፔን በምድቧ ከክሮሺያ ጋር በነበራት ግጥሚያ በ16 ዓመት ከ338 ቀናት እድሜው በመጫወት በውድድሩ ታሪክ የተሰለፈ በእድሜ ትንሹ ተጫዋች ክብረ ወሰንን መጨበጡ ይታወቃል።

በተጨማሪም ታዳጊው ስፔን ከጆርጂያ በነበራት የጥሎ ማለፍ ጨዋታ በ16 ዓመት ከ353 ቀናት እድሜው በመሰለፍ በውድድሩ ታሪክ በጥሎ ማለፍ ዙር የተጫወተ በእድሜ ትንሹ ተጫዋች መሆንም ችሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም