ስፔን በአውሮፓ ዋንጫ ፈረንሳይን ረታ ለፍጻሜ ደረሰች

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 2/2016(ኢዜአ)፦በ17ኛው የአውሮፓ ዋንጫ ተጠባቂ የግማሽ ፍጻሜ መርሐ ግብር ስፔን ፈረንሳይን 2 ለ 1 በማሸነፍ ለፍጻሜው ጨዋታ ደርሳለች።

በአሊያንዝ አሬና ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ በ9ኛው ደቂቃ ኪሊያን ምባፔ ከክንፍ ያሻገረውን ኳስ የ25 ዓመቱ የፓሪሰን ጀርሜን አጥቂ ራንዳል ኮሎ ሙዋኒ በግንባሩ በመግጨት ያስቆጠራት ግብ ፈረንሳይን መሪ አድርጎ ነበር።

ሙዋኒ በዘንድሮው የአውሮፓ ዋንጫ ለፈረንሳይ በክፍት የጨዋታ እንቅስቃሴ ግብ ያስቆጠረ የመጀመሪያው ተጫዋች ሆኗል።

የባርሴሎናው የክንፍ ተጫዋች ላሚን ያማል በ21ኛው ደቂቃ ከፍጹም ቅጣት ምት ክልል ውጪ በግሩም ሁኔታ ያስቆጠራት ግብ ስፔንን አቻ አድርጋለች።

ያማል በ16 ዓመት ከ362 ቀናት እድሜው ግብ በማስቆጠር በአውሮፓ ዋንጫ ታሪክ ኳስን ከመረብ ላይ ያሳረፈ በእድሜ ትንሹ ተጫዋች ሆኗል።

ስፔናዊው ታዳጊ በውድድሩ እስካሁን 3 ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ አቀብሏል።

የ26 ዓመቱ የአርቢ ላይፕዚግ የአጥቂ አማካይ ዳኒ ኦልሞ በ25ኛው ደቂቃ ያስቆጠራት ግብ ስፔንን ባለድል አድርጋለች።

ሁለተኛው የስፔን ጎል በመጀመሪያ በፈረንሳዊው የቀኝ መስመር ተጫዋች ጁሌስ ኩንዴ በራስ ላይ የተቆጠረ ግብ ተመዝግቦ የነበረ ቢሆንም የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ኦልሞ ለግቡ መቆጠር አብዛኛውን ድርሻ ወስዷል በሚል ግቡን በስሙ መዝግቦለታል።

ኦልሞ በአውሮፓ ዋንጫው ያስቆጠራቸውን ግቦች ወደ 3 በማሳደግ የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ለመሆን በመፎካከር ላይ ይገኛል።

ውጤቱን ተከትሎ የሶስት ጊዜ የአውሮፓ ዋንጫ አሸናፊዋ ስፔን ፍጻሜ የደረሰች የመጀመሪያ ሀገር ሆናለች። በፍጻሜው ከእንግሊዝና ኔዘርላንድ አሸናፊ ጋር ትጫወታለች።

ስፔን የዛሬውን ጨምሮ በአውሮፓ ዋንጫው 13 ግቦችን በማስቆጠር በውድድሩ በርካታ ጎሎችን ከመረብ ላይ ያሳረፈች ሀገር ናት።

በአንጻሩ የ2 ጊዜ የውድድሩ አሸናፊ ፈረንሳይ የደረጃ ጨዋታ ባለመኖሩ ምክንያት የጀርመን ቆይታዋ ዛሬ ፍጻሜውን አግኝቷል።

በ17ኛው የአውሮፓ ዋንጫ ሁለተኛ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ እንግሊዝና ኔዘርላንድ ከምሽቱ 4 ሰዓት በሲግናል ኢዱና ፓርክ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም