ለአንጋፋው የእግር ኳስ ሰው ኢንስትራክተር መንግሥቱ ወርቁ ሀገር አቀፍ መታሰቢያ ፕሮግራም ሊካሄድ ነው

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 2/2016(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያን በተጫዋችነትም በአሰልጣኝነትም ለአፍሪካ ዋንጫ እንድታልፍ ያደረገው አንጋፋው የእግር ኳስ ሰው ኢንስትራክተር መንግሥቱ ወርቁ ሀገር አቀፍ መታሰቢያ ፕሮግራም ሊካሄድለት ነው።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ወርቃማ ጊዜ ሲነሳ ስማቸው በቀዳሚነት ከሚጠቀሱ የአገር ባለውለታዎች መካከል ኢንስትራክተር መንግሥቱ ወርቁ አንዱ ነው።


 

መንግሥቱ ወርቁ በአፍሪካ ዋንጫ ታሪክ በተጨዋችነትም በአሰልጣኝነትም ኢትዮጵያን ለአፍሪካ ዋንጫ እንድታልፍ ማድረግ የቻለ የሀገር ባለውለታ ነው።

በ3ተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ኢትዮጵያ የውድድሩ አሸናፊ በመሆን ዋንጫ ስታነሳ 2 ጎሎች በማስቆጠርና የውድድሩ ኮከብ ተጨዋች በመሆንም በታሪክ መዝገብ ሰፍሮ ይገኛል።

ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን 102 ጊዜ ተሰልፎ 68 ጎሎችን ሲያስቆጥር በአፍሪካ ዋንጫ ታሪክ 10 ጎሎችን በማስቆጠር ከኮከብ ግብ አግቢዎች መካከል ነበር።


 

በአሰልጣኝነት ዘመኑም እአአ በ1982 በሊቢያ አዘጋጅነት በተካሄደው 13ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን በአሰልጣኝነት መርቷል።

ለዚህ የሀገር ባለውለታ ሀገር አቀፍ መታሰቢያ ፕሮግራም ለማካሄድ የአዲስ አበባ አሰልጣኞች ማህበር የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።

ለዚህም የቀድሞ ታዋቂ እግር ኳስ ተጨዋቾች፣ አሰልጣኞችና በተለያዩ የስፖርት ዘርፍ ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ግለሰቦች የተካተቱበት አስተባባሪ ኮሚቴ ተዋቅሮ እንቅስቃሴ ጀምሯል።

አስተባባሪ ኮሚቴውም በዛሬው ዕለት ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥቷል።

የኮሚቴው ዋና አስተባባሪና የኢትዮጵያ ብስክሌት ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ሠሎሞን በቀለ፤ የአገር ባለውለታዎችንና አንጋፋዎችን ማስታወስ ተገቢ መሆኑን ገልጸዋል።

ለዚህም ለአንጋፋው የእግር ኳስ ሰው ኢንስትራክተር መንግሥቱ ወርቁ ሀገር አቀፍ መታሰቢያ ፕሮግራም ለማካሄድ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ሀገር አቀፍ መታሰቢያ ፕሮግራሙ የኢንስትራክተር መንግሥቱ ወርቁን ሥራዎችና አስተዋጽኦ ለማስታወስ ትልቅ ዕድል እንደሚኖረውም ገልጸዋል።

የአፍሪካ ዋንጫን ኢትዮጵያ እንድታዘጋጅ እንቅስቃሴ በተጀመረበት በአሁኑ ወቅት ከሀገር አልፎ አህጉራዊ ስምና ዝና ያለውን መንግሥቱ ወርቁን ማስታወስ ተገቢ መሆኑን ተናግረዋል።

ለዚሁ መርሃ ግብርም የእግር ኳስ ውድድር፣ የስታዲየም መግቢያ ስያሜ፣ ዘጋቢ ፊልም ማዘጋጀት እና ሌሎችም ሁነቶች ይኖራሉ ብለዋል።

የኮሚቴው አባል የኢትዮጵያ ብሔራዊ በዱን የቀድሞ አሰልጣኝ ኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው፤ መንግሥቱ ወርቁ ኳስ ከመጫወትና ከማሰልጠን ባለፈ በሀገሪቱ የመጀመሪያውን የታዳጊዎች ፕሮጀክት ማስጀመሩን አስታውሰዋል።

መንግሥቱ ወርቁ በክለብ ታሪክ ከ1965 እስከ 1966 ዓ.ም ለስድስት ተከታታይ ዓመት ቅዱስ ጊዮርጊስን የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ ሻምፒዎና ዋንጫ አሸናፊ እንዲሁም በ1965 እና በ1966 ዓ.ም የጥሎ ማለፍ አሸናፊ ማድረግ ችሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም