ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) በሱዳን ወቅታዊ ጉዳይ ከጀነራል አብደል ፋታህ አል ቡርሃን ጋር ፍሬያማ ውይይት አድርገዋል- ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 2/2016(ኢዜአ)፦ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) በሱዳን ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከሱዳን ሉዓላዊ ሽግግር ምክር ቤት ሊቀመንበር ጀነራል አብደል ፋታህ አል ቡርሃን ጋር ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸውን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ  (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዛሬው እለት በሱዳን ይፋዊ የስራ ጉብኝት አድርገዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጉብኝት በማስመልከትም የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የጉብኝቱ አላማ በሱዳን የተከሰተው የእርስ በእርስ ግጭት በሰላማዊ መንገድ መቋጨት በሚቻልበት ጉዳይ ላይ ለመነጋገር መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዚህም የሁለቱ አገራት መሪዎች በወቅታዊ የሱዳን ጉዳይ ላይ ውጤታማ ውይይት ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ እና ሱዳን ከ744 ኪሎ ሚትር የሚዋሰኑ ጎረቤት አገራት መሆናቸውን ጠቅሰው ጠንካራ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት፣ የባህልና የምጣኔ ሃብት ትስስር ያላቸው አገሮች መሆናቸውን ገልጸዋል።

በመሆኑም የአንዱ አገር ችግር የሌላውንም የሚነካ በመሆኑ ለችግሮች የጋራ መፈትሄ በመሻት ለስኬቱም በጋራ መስራት ይኖርባቸዋል ብለዋል።

የሱዳን ተፋላሚ ሃይሎችም ልዩነቶቻቸውን በሰላማዊ መንገድ በመፍታት ለሀገራቸው ሰላም በጋራ እንዲሰሩ የተለያዩ ጥረቶችን ስታድርግ መቆየቷን አስታውሰው በቀጣይም ጥረቷን ትቀጥላለች ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከዚህ በፊትም የሱዳን ተፋላሚ ሃይሎች ለሱዳን ህዝብ ጥቅም ቅድሚያ በመስጠት ሰላም እንዲያወርዱ ሲያግባቡ መቆየታቸውን ጠቁመዋል፡፡

በዛሬው እለትም በሱዳን ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን ጋር ፍሬያማና የተሳካ ውይይት ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ የሱዳን ወቅታዊ ችግር በውይይት እንዲፈታ አስፈላጊውን ድጋፍና እገዛ ለማድረግ ዝግጁ መሆኗንም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አረጋግጠዋል።

የሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክርቤት ሊቀመንበር  ጀነራል  አብደል ፋታህ አል ቡርሃን፤ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጉብኘት ለሱዳን ህዝብ ያላቸውን ከበሬታ በተግባር ያረጋገጠ መሆኑን ተናግረዋል ብለዋል።

ለሱዳን ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እያደረጉት ላለው ጥረትም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም