ቀጥታ፡

በምክክር ሂደቱ ወጣቶች ንቁ ተሳታፊ መሆን  አለባችሁ - ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ  

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 2/2016(ኢዜአ)፦ በምክክር ሂደቱ ወጣቶች ንቁ ተሳታፊ መሆን  አለባችሁ ሲሉ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን "የወጣቶች ሚናና ተሳትፎ ለሀገራዊ ምክክር" በሚል መሪ ሀሳብ ያዘጋጀው የወጣቶች ምክክር መድረክ በአዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡

በመድረኩ ላይ በመገኘት መልእክት ያስተላለፉት የምክክር ኮሚሽኑ ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ፤ ለዘላቂ ሰላምና የተረጋጋ ሀገረ መንግስት ግንባታ የወጣቶች ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የረጅም ዘመን ታሪክ ከሀሳብ ልዕልና ይልቅ የተወሰኑ ቡድኖች ፍላጎት ጎልቶ በመውጣት ለልዩነትና ግጭት ሲዳርግ ቆይቷል ብለዋል።

ባለፉት ዘመናት የተወሰኑ ቡድኖች አንደበት ያላቸው ፖለቲከኞች ብቻ በመወሰን የዜጎችን ተሳትፎ በመንፈጉ መግባባት ርቆን ቆይቷል ሲሉም አንስተዋል።



በመሆኑም እየተንከባለሉ የመጡ ሀገራዊ ችግሮችን ተመካክሮ በዘላቂነት መፍታት እንደሚገባ ጠቅሰው በዚህ ረገድ ወጣቶች ንቁ ተሳታፊ መሆን አለባችሁ ሲሉ ተናግረዋል።

በሀገራዊ ምክክሩ በአጠቃላይ ሁሉም የማህበረሰብ ክፍሎች በሀገራቸው ጉዳይ ላይ መክረው የጋራ መግባባት የሚደርሱበት መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን ምክክር ያስፈልገናል ያሉት ፕሮፌሰር መስፍን፤ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ተወያይቶ የጋራ መግባባት ላይ መድረስ ያስፈልጋል ብለዋል።

በተለይም ወጣቶች በጋራ በመምከር ለመፍትሄውም መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ወጣቶች እስከምን ድረስ መሳተፍ እንዳለባቸው ቀድሞ ዝግጅት ማድረጉንም ገልጸዋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም