ቀጥታ፡

በክልሉ የ12ኛ ክፍል ፈተና ተፈታኞችን ከስነ ልቦና ዝግጅት ጀምሮ ለፈተና ለማብቃት ተሰርቷል---ቢሮው

ሆሳዕና፤ ሐምሌ 2/2016(ኢዜአ)፦በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተና ተፈታኞችን ከስነ ልቦና ዝግጅት ጀምሮ ለፈተና ለማብቃት በተደራጀ መልኩ ሲሰራ መቆየቱን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ። 

ቢሮው የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ዝግጅትን አስመልክቶ ዛሬ በወራቤ ከተማ መግለጫ ሰጥቷል።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር፣ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንተነህ ፈቃዱ እንደገለጹት፤ በክልሉ በ12ኛ ክፍል የገጠመውን የውጤት ማሽቆልቆል ለመቀየር ሲሰራ ቆይቷል።   

የዘንድሮ ተማሪዎችን በፈተናው ውጤታማ ለማድረግ ዕቅድ አውጥቶ በተደራጀና በተቀናጀ መልኩ ሲሰራ መቆየቱን የገለጹት ኃላፊው፣ ከስነ ልቦና ጀምሮ የተማሪዎችን አቅም ለመገንባት መሰራቱን ነው ያብራሩት።

ለተማሪዎች ተከታታይ አጋዥ ትምህርቶችን ከመስጠት ጎን ለጎን ክልል አቀፍ ሞዴል ፈተናን በመስጠት ለፈተናው የማብቃት ሥራው መሰራቱን ተናግረዋል።

በክልሉ ከ47 ሺህ 360 በላይ ተማሪዎች የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተና እንደሚወስዱና ለፈተናው ዝግጅት ስራው መጠናቀቁንም ገልጸዋል።

ከአጠቃላይ ተማሪዎች 32 ሺህ 131 የማህበራዊ ሳይንስ ተፈታኝ ተማሪዎች ወደ ተመደቡበት ዋቸሞ፣ ወልቂጤ፣ ወራቤ እና ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲዎች መጓጓዛቸውንም ተናግረዋል።

አቶ አንተነህ እንዳሉት፤ ከክልሉ አጠቃላይ ተፈታኞች ውስጥ 1ሺህ 401 የሚሆኑት ፈተናውን በበይነ መረብ የሚወስዱ ሲሆን፤ ቀሪዎቹ በወረቀት የሚፈተኑ ናቸው።

የዘንድሮው የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተና ከሐምሌ 3 እስከ 5 ቀን 2016 ዓ.ም እንደሚሰጥ ቀደም ሲል መገለጹ ይታወሳል። 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም