ቀጥታ፡

ተጎጂዎቹን መልሶ ለማቋቋም በሚከናወነው ተግባር አስፈላጊውን ድጋፍ እና እገዛ እናደርጋለን - የድሬዳዋ አገረ ስብከት ፅህፈት ቤት

ድሬዳዋ ፤ ሐምሌ 2/2016 (ኢዜአ)፦ በድሬዳዋ አሸዋ በሚባለው ገበያ በደረሰው የእሳት አደጋ የተጎዱ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም  በሚከናወኑ ተግባራት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ በኢትዮጵያ ኦሮቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የድሬዳዋ አገረ ስብከት ፅህፈት ቤት አስታወቀ።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የድሬዳዋ ሀገረ ስብከት ፅህፈት ቤት እና በየደረጃው የሚገኙ አድባራት እና ገዳማት የአመራር አባላት በድሬዳዋ አሸዋ ገበያ የደረሰውን የእሳት አደጋ ተዘዋውረው ተመልክተዋል።


 

የሀገረ ስብከቱ ስራ አስኪያጅ መልዓከ ኃይል አባ ተስፋዬ እማምሰው በወቅቱ እንደተናገሩት፤ በአደጋው የተጎዱ ወገኖችን አስተዳደሩ በጊዜያዊነት እና በዘላቂነት መልሶ ለማቋቋም የጀመራቸው ስራዎች የሚበረታቱ፣ ልዩ ድጋፍና መቀናጀት የሚጠይቁ ናቸው።

እነዚህን ወገኖች ለማቋቋም የሚከናወኑ ተግባራት ፍሬያማ እንዲሆኑ ቤተክርስቲያኒቷ በተለያዩ መንገዶች ምዕመናንን በማስተባበር ገቢ በማሰባሰብ ኃላፊነቷን እንደምትወጣ ተናግረዋል።

አደጋው ከተከሰተ ከሰኔ 25 ቀን 2016 ዓ.ም ማግስት ጀምሮ በድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር  የሚመራ  ዐቢይ ኮሚቴ እና የተለያዩ ንዑሳን ኮሚቴዎች ተቋቋመው ተጎጂዎችን በጊዜያዊነት እና በዘላቂነት ለማቋቋም የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል።


 

የገቢ አሰባሳቢ ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ሙሉካ መሐመድ በበኩላቸው፤ በድሬዳዋ የሚገኙ የሁሉም ኃይማኖት ተከታዮች ተጎጂዎችን መልሶ በማቋቋም ስራ ውስጥ በተደራጀ መንገድ ለመሳተፍ እያደረጉ የሚገኙት ተግባራት የሚበረታታ እና የሚመሰገን ነው።

ተጎጂዎችን በጊዜያዊነት እና በዘላቂነት ለማቋቋም የሚያስችሉ ድጋፎች የማሰባሰቡ ሥራዎች መጀመራቸውንም አክለዋል። 

 
 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም