የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ከአካባቢ ጥበቃ ባሻገር ለስራ ዕድል ፈጠራ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 2/2016(ኢዜአ)፦ የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ከአካባቢ ጥበቃ ባሻገር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና ለዜጎች የስራ ዕድል ፈጠራ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ  መሆኑ ተገለጸ።

በአዲስ አበባ የጉለሌ  ክፍለ ከተማ አመራሮችንና የክፍለ ከተማው ነዋሪዎች እንጦጦ ፓርክ የአረንጓዴ አሻራ መረኃ ግብር አካሂደዋል።

የክፍለ ከተማው ዋና ስራ አስፈፃሚ ወልዴ ወገሰ፤ ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ቀደም ብሎ ችግኞችን በማፍላት የመትከያ ጉድጓዶችም መዘጋጀታቸውን አስታውሰዋል።

አሁን ላይ ደግሞ የክፍለ ከተማውን ሰራተኞችና ነዋሪዎችን በማሳተፍ ችግኞችን መትከል መጀመራቸውን ገልፀዋል።

የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ከአካባቢ ጥበቃ ባሻገር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና ለዜጎች የስራ ዕድል ፈጠራ ከፍተኛ አስተዋጽ እያበረከተ መሆኑን ጠቅሰው በቀጣይም የመትከልና የመንከባከብ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል። 


 

የጉለሌ ክፍለ ከተማ የብልፅግና ፓርቲ  ጽህፈት ቤት  ሃላፊ ይከበር  ስማቸው፤ በአረንጓዴ አሻራ መረሃ ግብር የአየር ንብረት ለውጥን  የሚቋቋም ሀገር የመገንባት ስራውን ለማሳካት በትብብር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡


 

  በመርሀ ግብሩ ላይ ከተሳተፉ አስተያየት ሰጭዎች መካከል አሸናፊ ቦረና እና ኤልሳቤት ጌትነት፤ አሻራቸውን በማሳረፋቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።

በመሆኑም ችግኞችን ከመትከል ባለፈ በየጊዜው በመንከባከብ ለፍሬ እንዲበቁ የሚሰሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

 

    

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም