ቀጥታ፡

ወጣቶች የመነጋገርና የመደማመጥ ባህልን በማጎልበት በሀገራዊ ምክክሩ ሚናቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 2/2016(ኢዜአ)፦ ወጣቶች የመነጋገርና የመደማመጥ ባህልን በማጎልበት በሀገራዊ ምክክሩ ሚናቸውን እንዲወጡ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ጥሪ አቀረቡ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ያዘጋጀው የወጣቶች የውይይት መድረክ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል።

ውይይቱ እየተከናወነ የሚገኘው "የወጣቶች ሚናና ተሳትፎ ለሀገራዊ ምክክር" በሚል መሪ ቃል ነው።

የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መሥፍን አርዓያ፤ በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር ወጣቶች የመነጋገርና የመደማመጥ ባህልን በማጎልበት በሀገራዊ ምክክሩ ሚናቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡

ለሰላምና ለተረጋጋ የሀገረ መንግስት ግንባታ የወጣቶች ሚና ከፍተኛ መሆኑንም ተናግረዋል።


 

በመድረኩ በትውልዶች መካከል መኖር ስለሚገባው ምክክር እንዲሁም በሀገራዊ ምክክሩ የወጣቶችን ሚና ማሳደግ ስለሚቻልባቸው መንገዶች በኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች የውይይት መነሻ ሀሳብ ቀርቦ ውይይት እየተደረገ ነው።

እየተካሄደ በሚገኘው ውይይት ከመላ ሀገሪቱ የመጡ ከ200 በላይ ወጣቶች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሶስተኛ ምዕራፍ አካል የሆነ የአጀንዳ ልየታ የምክክር ምዕራፍ በግንቦት ወር 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ ማካሄዱ የሚታወስ ነው።

የማህበራትና ተቋማት ተወካዮች፣ የመንግስት ተወካዮች፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎችና ከተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች እንዲሁም የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍል ተወካዮች የተመረጡ ወኪሎች የተሰበሰቡ አጀንዳዎችን በማደራጀት በምክክሩ ላይ አቅርበዋል።

በቀጣይ በሌሎች ክልሎችና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት እንደሚከናወን ከኮሚሽኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም