ቀጥታ፡

ለቀጣይ አምስት ዓመታት ተግባራዊ የሚሆን የምግብ ደኅንነት ፍኖተ-ካርታ ተዘጋጀ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 2/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ የምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን  ለቀጣይ አምስት ዓመታት ተግባራዊ የሚሆን  የምግብ ደኅንነት ፍኖተ-ካርታ አዘጋጀ።  

በባለሥልጣኑ የምግብ ደኅንነትና የሥርዓተ-ምግብ አማካሪ የሆኑት ወንዳፍራሽ አበራ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የምግብ ወለድ በሽታን በዘላቂነት ለመከላከል የሚያስችል ፍኖተ-ካርታ ተዘጋጅቷል። 

ፍኖተ-ካርታው የአፍሪካ ኅብረት ኢትዮጵያን ጨምሮ የ12 የአፍሪካ አገራትን በመምረጥ የምግብ ደኅንነት ፍኖተ-ካርታ እንዲያዘጋጁ ባቀረበው ሃሳብ መሠረት መዘጋጀቱንም ነው የጠቆሙት።

ፍኖተ-ካርታው የዓለም ጤና ድርጅትና የዓለም የምግብና እርሻ ፕሮግራም በትብብር በቀረጹት የመረጃ መሰብሰቢያ መጠይቅ እንዲሁም በአገሪቱ የሚመለከታቸው አካላት ባስቀመጡት አቅጣጫ መሰረት መዘጋጀቱንም ጠቁመዋል። 

ሰነዱንም ለማዘጋጀት ከ11 የሚበልጡ በአገር ውስጥ የሚገኙ ተቋማት መሳተፋቸውን ጠቅሰዋል። 

ለአብነትም ግብርና ሚኒስቴር፣ ጤና ሚኒስቴር፣ ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ የምርምር ተቋማት፣ ሌሎች የግል የምግብ ላቦራቶሪዎችና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በፍኖተ-ካርታ ዝግጅቱ መሳተፋቸውን ጠቁመዋል።

የፍኖተ-ካርታው ትግበራ ሰዎች በምግብ ወለድ በሽታ ሊከሰትባቸው የሚችለውን የጤና እክል መቀነስ፣ ምርቶች የሚጓጓዙበትን ሰንሰለት የማመቻቸትና በክምችትና በማጓጓዝ ሂደት የሚበላሹ ምግቦችን የመቀነስ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ገልጸዋል። 

በፍኖተ-ካርታው የሰው ኃይልና ግብዓት አቅርቦት፣ የቁጥጥር ተግባር፣ ቅንጅታዊ አሠራር፣ እውቀትና ክህሎት፣ ጥናትና ምርምር እንዲሁም ቀጣይነት ያላቸው ተግባራትን የሚያካትት ይዘት እንዳለውም ነው ያመላከቱት።

በፍኖተ-ካርታው ቅንጅታዊ አሠራር፣ የፖሊሲና ሕጎች አተገባበር የግብዓት አቅርቦትና የመሳሰሉት ስድስት ስትራቴጂክ ዓላማዎች መዘጋጀታቸውን ጠቁመው፤ ተቋማት የድርሻቸውን በመውሰድ ለተግባራዊነቱ ይሠራሉ ነው ያሉት።

 ለተከታታይ አምስት ዓመት ተግባራዊ ለሚደረገው ለዚሁ ፍኖተ-ካርታ 338 ሚሊየን ዶላር በጀት መመደቡንም ጠቅሰዋል።


 

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የገበያና ፋብሪካ ምርቶች ጥራት ማረጋገጥ ዴስክ ኃላፊ ተከተል ጌቱ፤ የምግብ ደኅንነትን ለመጠበቅ ምርት ከአምራቹ እስከ ተጠቃሚው እስኪደርስ ጥራትና ደኅንነቱ እንዲጠበቅ የቁጥጥር ሥራ የማከናወን ድርሻ እንዳላቸው ነው የገለጹት።

ይህንንም ተከትሎ ተቋሙ በፍኖተ-ካርታው የተሰጠውን ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።  

የኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን የእንስሳት ምርት ሬጉላቶሪ መሪ ሥራ አስፈጻሚ አያሌው ሹመት(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ከዚህ ቀደም ፍኖተ-ካርታው ባለመኖሩ የአተገባበር ክፍተቶች እንደነበሩባቸው ገልጸዋል።


 

የሰነዱ መዘጋጀት መንገድ ከማሳየት ባሻገር ውጤታማ ሥራ ለመሥራት እንደሚያስችላቸው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም