በክልሉ በዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለፍራፍሬ ችግኞች የተለየ ትኩረት ተሰጥቷል-አቶ እንዳሻው ጣሰው

ዱራሜ ፤ ሐምሌ 1/2016 (ኢዜአ)፡- በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ለሚያግዙ የፍራፍሬ ችግኞች የተለየ ትኩረት መሰጠቱን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው ገለጹ።

ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው "የምትተክል ሀገር የሚያጸና ትውልድ" በሚል መሪ ሐሳብ የሚካሄደውን ክልል አቀፍ የዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በካምባታ ዞን ዱራሜ ከተማ ተገኝተው አስጀምረዋል።


 

ርዕሰ መስተዳድሩ በእዚህ ወቀት እደገለጹት በክልሉ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተጀመሩ ስራዎችን ለማገዝ ለፍራፍሬ ልማት ትኩረት ተሰጥቷል።

ለዚህም የሚያግዙ የተለያዩ የፍራፍሬ ችግኞች በልዩ ሁኔታ ተዘጋጅተው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የችግኝ ተከላ ሥራ በይፋ መጀመሩን አውስተዋል።

ይህም ከሁለት ዓመት ባጠረ ጊዜ የክልሉን ምርታማነት በማሳደግ ከተረጂነት ለመውጣት የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት ያግዛል ብለዋል።

ዛሬ በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ዱራሜ ካምፓስ የተጀመረው የአቦካዶ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በሌሎችም ተቋማት እንዲሰፋ ይደረጋል ነው ያሉት።


 

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ክላስተር አስተባባሪና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር በበኩላቸው በክልሉ ባለፉት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተተከሉ ችግኞች ምርታማነት ላይ ለውጥ እንዲመጣ አስችለዋል ብለዋል።

ዘንድሮ ለምግብነት የሚውሉ፣ ገቢን ለማሳደግ፣ ለአፈር ጥበቃና ለሌሎች አገልግሎቶች የሚውሉ ችግኞች እንደሚተከሉ ተናግረዋል።

በአረንጓዴ አሻራ ከሚተከሉት 60 በመቶው የሚሆነው የፍራፍሬ ችግኝ መሆናቸውንም አስረድተዋል።

ይህም ከተረጂነት ለመውጣት የሚደረገውን ጥረት ያግዛል፤ የዜጎችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትንም ለማረጋገጥ እድል ይሰጣል ብለዋል አቶ ኡስማን።

በመሆኑም ሁሉም የክልሉ ነዋሪ ቀደም ሲል ሲያደርገው እንደነበረው በክረምት የችግኝ ተከላ መርሀግብር በነቂስ ወጥቶ ተሳትፎውን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።

በችግኝ ተከላው ከተሳተፉት የአካባቢው ነዋሪዎች መካከል አቶ አማኑኤል ያዕቆብ ከዚህ ቀደም የተተከሉ ችግኞች ለውጥ እያመጡ መሆናቸውን ጠቁመው፣ በቀጣይ ይህን በማጠናከር በምግብ ራሳችንን ለመቻል በጋራ መትጋት ይገባል ብለዋል።

በተለይ ለፍራፍሬ ልማት ትኩረት መሰጠቱ ሁሉንም ስለሚያነሳሳ ዛሬ የተተከሉ የአቦካዶ ችግኞች በመንከባከብ ለፍሬ እንዲበቁ ሃላፊነታችንን እንወጣለን ብለዋል  

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ ተመስገን ጊቻሞ በበኩላቸው ችግኝ መትከል የሚያስገኘው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ስለተረዳን በዘንድሮም የችግኝ ተከላ በነቂስ እየተሳተፍን ነው ብለዋል።

ችግኝ ከመትከል ባለፈ ለፍሬ እንዲበቃ ማድረግ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

በክልል አቀፍ የችግኝ ተከላ ማስጀመሪያ ላይ የክልሉ እና በክልሉ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎችና ሌሎች ተቋማት ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎችና የአካባቢው ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም