ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የንግዱ ዘርፍ በአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ተወዳዳሪ ለመሆን ለምርት ጥራትና ለዲጂታል ግብይት ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ ተመላከተ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 1/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የንግዱ ዘርፍ በአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ተወዳዳሪ ለመሆን ለምርት ጥራትና ለዲጂታል ግብይት ትኩረት ሊሰጡ እንደሚገባ በዲጂታል ግብይት የተሰማሩ አገልግሎት ሰጪዎች ተናገሩ።

የዲጂታል የክፍያ ስርዓት በአህጉር ደረጃ ለሚከናወነው ግብይት አስፈላጊ በመሆኑ የክፍያ ስርዓትን በማዘመን በኩል የተጀመሩ ተግባራት መጠናከር እንዳለባቸውም ጠቁመዋል።

የአፍሪካ ነጻ አህጉራዊ የንግድ ቀጣና ስምምነት በ2010 ዓ.ም በሩዋንዳ ኪጋሊ በተካሄደ የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በ44 ሀገራት መፈረሙ ይታወሳል።

ስምምነቱ በአፍሪካ ሀገራት መካከል የሚደረገውን ንግድ የሚያሳልጥና በአጀንዳ 2063 “የተዋሃደች፣ የበለፀገች፣ ሰላማዊ አፍሪካን” ለመፍጠር ያለመው የፓን አፍሪካ ራዕይ ላይ የተመሰረተ ነው።

ስምምነቱ የአፍሪካን አህጉር የኢኮኖሚያዊ ውህደት የሚያጠናክርና በሀገራት መካከል ኢንቨስትመንትን ለማመቻቸት ያለመ ነው።

በሞባይል መተግበሪያና በድረገፅ በሚቀርብ የደንበኛ ትዕዛዝ አስቤዛን ቤት ለቤት የማድረስ ስራ እየሰራ የሚገኘው የአስቤዛ ዋና ስራ አስፈፃሚ በረከት ታደሰ ለኢዜአ እንዳሉት በኢትዮጵያ የኤሌክትሮኒክ ንግድ (E-commerce) ባህል አላደገም።

ስለሆነም የግብይት ስርዓቱን በዲጅታል በማዘመን በአፍሪካ ደረጃ ለሚደረገው ግብይት መሻሻል ይገባል ብለዋል።

የኢትስዊች የክፍያ ስርዓት አማካሪ አብርሃም ካሳሁን በበኩላቸው ኢትስዊች በኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ባለቤትነት የሚመራና ክፍያን በቀላሉ በባንኮች መካከል ማካሄድ የሚያስችል ነው።

ኢትስዊች በባንኮች መካከል ያለውን ትስስር ከማጠናከር ባለፈ በአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ቀልጣፋ የክፍያ ስርዓትን ለመፍጠር እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

አስተያየት ሰጪዎቹ አክለውም የሀገር ውስጥ ድርጅቶች በነፃ የንግድ ቀጣናው ተወዳዳሪ ለመሆን ለምርት ጥራት፣ ለዲጅታል ግብይትና ማስታወቂያ ትኩረት እንዲሰጡም ጠይቀዋል።

በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የዲጂታል ኢኮኖሚ ልማት መሪ ስራ አስፈፃሚ ስዩም መንገሻ መንግስት በዲጂታል ግብይትና በሌሎች ስራዎች የግሉን ዘርፍ መሪነት ለማረጋገጥ ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና በዲጂታል ግብይት የሚሰማሩ ድርጅቶች ማሟላት በሚገባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ከግሉ ዘርፍ ጋር በመምከር ያሉ ችግሮችን ለመፍታት እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም