ቀጥታ፡

የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተከናወኑ የሚገኙ አበረታች ስራዎች ማስቀጠል ይገባል- አምባሳደር ነቢል ማህዲ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 1/2016(ኢዜአ):- በሀረሪ ክልል የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተከናወኑ የሚገኙ ዘርፈ ብዙ አበረታች የልማት ስራዎችን ማስቀጠል እንደሚገባ በደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር ነቢል ማህዲ ገለፁ።

በ26ኛ አለም አቀፍ የሀረር ቀን ለመሳተፍ ሀረር ከተማ የተገኙት አምባሳደሩ በክልሉ እየተከናወኑ በሚገኙ ሁሉን አቀፍ ስራዎች መደሰታቸውን ጠቅሰዋል።

በክልሉ በተለይ በከተማም ሆነ በገጠሩ አካባቢ በመሰረተ ልማት ዘርፍ እየተሰሩ የሚገኙ ውጤታማ ስራዎች የህዝብን ጥያቄ በመመለስና ፍትሃዊነትን በማረጋገጥ ረገድ ሚናቸው የጎላ ሆኖ እንዳገኙት አንስተዋል።

የሀረር ከተማ በአገሪቱ ካሉ የቱሪዝም መዳረሻዎች አንዷ ነች ያሉት አምባሳደሩ፤ በከተማው ያሉ የቱሪዝም መዳረሻዎች በተለይ አለም አቀፍ ቅርስ የሆነውን የጁገል ቅርስ ለጎብኚዎች ምቹ እንዲሆን በማድረግ የተከናወነው የመልሶ ማልማት ስራ የቱሪስት ፍሰቱን የሚያሳድግ መሆኑን አስረድተዋል።

ይህም ዘርፉን ከማሳደግና ህዝብን ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ አደራን ጠብቆና ተንከባክቦ ለመጪው ትውልድ የማስተላለፍ ኃላነፊት በአግባቡ የመወጣት ተግባር ነው ብለዋል።

ከመደመር ትውልድ መፅሀፍ ሽያጭ በተገኘው ገቢ እና ማህበረሰቡን በማሳተፍ በሀረር ከተማ የተገነባው የሀረር ኢኮ ፓርክ በክልሉ በቱሪዝም ዘርፍ ያለው እምቅ ሀብት ለመጠቀም ከፍተኛ ትኩረት እንደተሰጠው አንዱ አመላካች መሆኑን ገልፀዋል።

በክልሉ በኮሪደር ልማት፣ በመንገድ መሰረተ ልማት እና ከተማዋን ፅዱ እና አረንጓዴ ለማድረግ እየተከናወኑ የሚገኙ ስራዎች ተስፋ ሰጪ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

በክልሉ የተለያዩ የሰላም አደረጃጀቶችን በመፍጠር ፤ የወንድማማችነት እሴቶች እና አብሮነትን ለማጎልበት የተሰጠው ትኩረት በቀጣይም ማስቀጠል ወሳኝ እንደሆነ ነው የተናገሩት።

በክልሉ የህዝብን ተጠቃሚነት ለማጎልበት እየተሰሩ የሚገኙ አበረታች የልማት ስራዎች አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል ማለታቸውንም የክልሉ ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት መረጃ ያመለክታል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም