ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ሀገሩን ከብተና የታደገ በአለም ሠላም ማስከበር ትልቅ ታሪክ ያለው ሠራዊት ያላት ሀገር ናት- ሌተናል ጄኔራል ዘውዱ በላይ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 1/2016(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ሀገሩን ከብተና የታደገ በአለም ሠላም ማስከበር ትልቅ ታሪክ ያለው ሠራዊት ያላት ሀገር ናት ሲሉ የማዕከላዊ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ዘውዱ በላይ ገለጹ።

ሌተናል ጄኔራል ዘውዱ በመከላከያ ዋር ኮሌጅ ተገኝተው በውጊያ ዘመቻ ፅንሰ ሃሳብና በአለም አቀፋዊ፣ አካባቢያዊና ሀገራዊ፣ ስትራቴጂካዊ የደህንነት ጉዳዩች ዙሪያ እውቀታቸውን እና የአመራር ልምዳቸውን ለ2ኛ ዙር ተመራቂዎች እና ለአጭር ኮርስ ተማሪዎች እንዲሁም ለስታፍ አመራሮች አካፍለዋል።


 

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ከጥንት ጀምሮ የፖለቲካ ድርጀቶች ቢቀያየሩም ሰራዊቱ ግን እንደ ሰራዊት ፀንቶ በመቆም ሀገርን ያፀና ታማኝ ሃይል ነው ሲሉም ሌተናል ጄኔራል ዘውዱ ገልጸዋል።

ሠራዊቱ ኢትዮጵያን ከብተና የታደገ ከሀገሩ አልፎ በአለም ሰላም ማስከበር ከፍተኛ አስተዋፀኦ ያበረከተ ሠራዊት ነው ብለዋል።

ጦርነት የሚጀመረው አንዱ ከአንዱ እበልጣለሁ የውጊያና የጦርነት ልምድ አለኝ ብሎ ከትምክህትና ከእብሪት ከሚነሳ አካል እንዲሁም ልዩ ጥቅም እናገኛለን በሚሉ የውጭ ጣልቃ ገብ ሃይሎች አለፍ ሲልም በፍትህ መዛባት ሰበብ እንደሆነ ጄኔራል መኮንኑ አስገንዝበዋል፡፡

ጦርነት በቅንጅት የሚመራና አቅም የሚጠይቅ በመሆኑ እንደ ዋር ኮሌጅ ያሉ የትምህርት ማዕከላት በሀገራችን መፈጠራቸው በስነ-ጦርነት ብቃትና እውቀት ያላቸው ስትራቴጂክ መሪዎች እንዲፈጠሩ ያደርጋሉ ሲሉም ገልጸዋል።

በዋር ኮሌጅ ተምረውና ተመርቀው ወደ ስራ የሚገቡ ስትራቴጂክ አመራሮች ሠራዊታችን በስነ-ልቦናና በአመራር ብቃቱ ዳብሮ የማድረግ አቅሙን ከፍ ማድረግ እንዲችል የሚያግዝ መሆኑን ማስገንዘባቸውን ከመከላከያ ሰራዊት የማህበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም