መከላከያ ሠራዊት ሀገር ከማጽናት በተጓዳኝ በበጎ ፈቃድ ስራዎች ሕዝብ የማገልገል ተግባሩን አጠናክሮ ይቀጥላል- ሌተናል ጀነራል ሹማ አብደታ - ኢዜአ አማርኛ
መከላከያ ሠራዊት ሀገር ከማጽናት በተጓዳኝ በበጎ ፈቃድ ስራዎች ሕዝብ የማገልገል ተግባሩን አጠናክሮ ይቀጥላል- ሌተናል ጀነራል ሹማ አብደታ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 1/2016(ኢዜአ)፦ መከላከያ ሠራዊት የሕይወት መስዋዕትነት በመክፈል ሀገር ከማጽናት በተጓዳኝ በበጎ ፈቃድ ስራዎች ሕዝብ የማገልገል ተግባሩን አጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ የኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ አዛዥ ሌተናል ጀነራል ሹማ አብደታ ተናገሩ።
በመከላከያ ሰራዊት የኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ፣ የባሕር ኃይልና የብሔራዊ ተጠባባቂ ኃይል የጦር ክፍሎች በጋራ በመሆን ለአንድ ወር የሚቆይ የክረምት በጎ ፈቃድ መርሐ ግብር በይፋ አስጀምረዋል።
በጎ ፈቃድ ስራው ትምህርት ቤቶችን መገንባት፣ የደም ልገሳ፣ የአቅመ ደካሞችን ቤት ዕድሳት እንዲሁም ከሰራዊቱ የወጡና የሕይወት መስዋዕትነት ለከፈሉ አባላት ቤተሰቦች ድጋፍ እንደሚደረግ ተገልጿል፡፡
በመርሐ ግብሩ ላይ የዕዙ አዛዥ ሌተናል ጀነራል ሹማ አብደታ፣ የባሕር ኃይልና የብሔራዊ ተጠባባቂ ኃይል ተወካዮችን ጨምሮ የመከላከያ ጀኔራል መኮንኖችና የሰራዊቱ አባላት ተገኝተዋል።
የክረምት በጎ ፈቃድ መርኃ ግብሩ "ከካምፓችን ወደ ህዝባችን" በሚል መሪ ሀሳብ ከሐምሌ 1 ቀን እስከ 30 ቀን 2016 ዓ.ም የሚቆይ ነው።
የኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ አዛዥ ሌተናል ጀነራል ሹማ አብደታ በዚህ ወቅት እንዳሉት ሰራዊቱ በበጎ ፈቃድ መርሐ ግብሩ ከካምፕ ባሻገር ከህብረተሰብና ከመንግስት ጋር በመሆን በስፋት ይሳተፋል ብለዋል።
ሠራዊቱ በሕይወት መሰዋዕትነት ሀገር ከማጽናት ጎን ለጎን በበጎ ፈቃድ ስራዎች ሕዝብ የማገልገል የተለመደ ተግባሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
ደም ልገሳን ጨምሮ በክረምት መርሐ ግብር የሚከናወኑ ስራዎች ኮሚቴ ተዋቅሮ ወደስራ መገባቱን ተናግረዋል።
በአረንጓዴ አሻራ የቀደመ ልምዱን በማጠናከር ሰራዊቱ በተሰማራባቸው ቀጣና ሁሉ በአንድ ዕጁ ሰላም፣ በአንድ ዕጁ አረንጓዴ ልማት ያከናውናል ሲሉም አክለዋል።
ሰራዊቱ መንግስት በምግብ ራስን ለመቻል እያደረገ ባለው ጥረት አጋር በመሆን በግብርናው ዘርፍ ትልቅ ስራ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ፣ ባሕር ኃይል፣ የብሔራዊ ተጠባባቂ ኃይል የጦር ክፍሎች ከካምፓቸው ጀምሮ እስከ ተሰማሩበት አካባቢ ሁሉ የተለያዩ በጎ ተግባራትን ያከናውናሉ ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሰላም፣ ልማትና ክብር እንዲጠበቅ ሰራዊቱ አስተማማኝ ዘብ መሆኑን ገልጸው፤ ሰራዊቱ ባለበት ሁሉ በመርሐ ግብሩ በጎ ስራውን እንዲያጎለብት ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።
የባሕር ኅይል አባል የሆኑት ኮማንደር ሀብታሙ እሸቱ ሰራዊቱ ደም በመለገስ የሌሎችን ሕይወት የማዳን በጎ ተግባር የማከናወን ልምድ እንዳለው ጠቅሰው ይህንን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
የኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ አባል ሌተናል ኮሎኔል ገብረጻድቅ ገብረእግዚአብሄር ደም መለገስ ሕይወቱን ለሀገርና ህዝብ ልዓላዊነት ለሚሰዋ ሰራዊት ትንሹ አስተዋጽኦ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በዚህም ደም መለገስን ጨምሮ በቀጣይ የክረምት በጎ ፈቃድ ተግባራት ሁሉ በንቃት እንደሚሳተፉ ተናግረዋል።