ፖላንድ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ምጣኔ ኃብታዊ አጋርነት ይበልጥ ለማጠናከር ትሰራለች - ኢዜአ አማርኛ
ፖላንድ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ምጣኔ ኃብታዊ አጋርነት ይበልጥ ለማጠናከር ትሰራለች
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 1/2016(ኢዜአ)፦ ፖላንድ ምጣኔ ኃብትን ጨምሮ በሌሎች የትብብር መስኮች ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትብብር ለማጠናከር እየሰራች መሆኑን በኢትዮጵያ የሀገሪቱ አምባሳደር ፕርዝማይዝለው ቦባክ ገለጹ።
ምንም እንኳን የኢትዮጵያና የፖላንድ ግንኙነት የጀመረው በ1920ዎቹ ቢሆንም ይፋዊ ዲፕሎማሲያዊ የሁለትዮሽ ግንኙነት የተጀመረው ግን እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1945 ነበር።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1963 ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በፖላንድ ያደረጉት ጉብኝት የሁለቱ ሀገራት ግንኙነትን ወደ ላቀ ደረጃ በማድረስ ትልቁን ሥፍራ እንደሚይዝም ተገልጿል።
ይህንንም ተከትሎ በተለያዩ ጊዜያት በሚደረጉ የሁለትዮሽ ውይይቶችና በከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ደረጃ በሚደረጉ ጉብኝቶች የሀገራቱ ግንኙነት ይበልጥ እየተጠናከረ መጥቷል።
ከዚህ አንጻር፤ የኢፌዴሪ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) ወደ ፖላንድ በማቅናት ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን በአንጻሩ፤ የፖላንድ ፕሬዝዳንት አንሬዜጅ ዱዳም ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት በጋራ ጉዳዮች ላይ መምከራቸው ይታወሳል።
ይህንንም ተከትሎ ሁለቱ ሀገራት በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ እንዲሁም በማኅበራዊ መስኮች በትብብር ሲሰሩ መቆየታቸውን ነው በአዲስ አባበ የሚገኘው የፖላንድ ኤምባሲ መረጃ የሚያሳየው።
በኢትዮጵያ የፖላንድ አምባሳደር ፕርዝማይዝለው፤ በተለያዩ የትብብር መስኮች ላይ የተመሠረተውንና በርካታ ጊዜያትን ያስቆጠረውን ይህንን አጋርነት ይበልጥ ለማጠናከር እየተሰራ ነው ብለዋል።
ፖላንድና ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ፣ በሳይንስ፣ በባህልና ሥነ-ጥበብ፣ በመሠረተ-ልማትና በሌሎች መስኮች በትብብር መሥራት የሚችሉበት በርካታ ዕድሎች መኖራቸውንም ነው የገለጹት።
በቅርቡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ፖላንድ ርዕሰ መዲና ዋርሶው የጀመረው የቀጥታ በረራ የሁለቱን ሀገራት የንግድና ኢንቨስትመንት ትስስር ወደ ላቀ ደረጃ ለመውሰድ ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረውም ጠቅሰዋል።
አሁን ላይ ሁለቱ ሀገራት ጠንካራ የፖለቲካ ትብብር እንዳላቸው ያነሱት አምባሳደሩ፤ ምጣኔ ኃብታዊ አጋርነቱን በቅድሚያ ከዚያም የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱን ይበልጥ ለማጠናከር በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ነው ያረጋገጡት።