በክልሉ በሚከናወኑ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን እንዲሳተፉ ጥሪ ቀረበ

ሐረር ፤ ሐምሌ 1/2016 (ኢዜአ)፦ በክልሉ በሚከናወኑ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራት ላይ  ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን እንዲሳተፉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር  ኦርዲን በድሪ ጥሪ አቀረቡ። 

ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ጥሪውን ያስተላለፉት 26ኛው ዓለም አቀፍ የሐረር ቀን በዓልን ምክንያት በማድረግ ዛሬ በክልሉ የተገነቡ የልማት ፕሮጀክቶች በተመረቁበት ወቅት ነው።

ርዕሰ መስተዳድሩ እንደተናገሩት በዓሉን ምክንያት በማድረግ ከወጣው መርሃ ግብር መካከል ነገ በክልሉ "የበጎ ፈቃድ ቀን" ተብሎ መያዙን ተናግረዋል።

የበጎ ፈቃድ ቀኑም እርስ በርስ የምንደጋገፍበት፣ የምንረዳዳበት እና በጎ ስራዎችን የምናከናውንበት እለት ነው ብለዋል።

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራዎችን ማከናወን የህሊና እርካታ የሚሰጥ መልካም ተግባር መሆኑንም አክለዋል፡፡

በክልሉ መደገፍ እና መረዳት የሚገባቸው በርካታ ግለሰቦች እንዳሉ ገልጸው፤ በዚያው ልክ መጠናከር የሚገባቸው የልማት ስራዎችም መኖራቸውን ጠቁመዋል።

በዚህ ላይ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በዚህ መሰል ተግባራት ላይ እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።

26ኛው ዓለም አቀፍ የሐረር ቀን በዓልን ምክንያት በማድረግ ውጭ የሚኖሩ በርካታ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያውን ወደ ክልሉ መምጣታቸው ይታወቃል።

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም