ቀጥታ፡

የኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ፣ የባሕር ኃይልና የብሔራዊ ተጠባባቂ ኃይል የክረምት በጎ ፈቃድ መርሐ ግብርን አስጀመሩ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 1/2016(ኢዜአ)፦ በአገር መከላከያ ሰራዊት የኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ፣ የባሕር ኃይልና የብሔራዊ ተጠባባቂ ኃይል የጦር ክፍሎች ለአንድ ወር የሚቆይ የክረምት በጎ ፈቃድ  መርሐ ግብር በይፋ አስጀመሩ።

በመርሐ ግብሩ ላይ የዕዙ አዛዥ ሌተናል ጀኔራል ሹማ አብደታ፣ የባሕር ኃይልና የብሔራዊ ተጠባባቂ ኃይል ተወካዮችን ጨምሮ የመከላከያ ጀነራል መኮንኖችና የሰራዊቱ አባላት ተገኝተዋል። 

የክረምት በጎ ፈቃድ መርኃ ግብሩ "ከካምፓችን ወደ ህዝባችን" በሚል መሪ ቃል ከሐምሌ 1 ቀን እስከ 30 ቀን 2016 ዓ.ም የሚቆይ ነው።

የኮማንዶና አየር ወለድ ዕዙ አዛዥ ሌተናል ጀነራል ሹማ አብደታ በዚህ ወቅት የበጎ ፈቃድ ስራው "ከካምፓችን ወደ ሕዝባችን "በሚል መሪ ቃል ከካምፕ ጀምሮ እስከ ህብረተሰብ የሚዘልቅ አካባቢን ውብና ፅዱ የማድረግ ስራን ዓላማው ያደረገ ነው ብለዋል። 

በአረንጓዴ ልማት ረገድም ከዚህ በፊት የነበረውን ልምድ በማጠናከር ይበልጥ በአርአያነት ይሰራል ነው ያሉት።

ሰራዊቱ በተሰማራባቸው ቀጣና ሁሉ በአንድ ዕጁ ሰላም፣ በአንድ ዕጁ አረንጓዴ ልማት ያከናውናል ሲሉም አክለዋል።

የአቅመ ደካሞችን ቤት ዕድሳት በተመለከተም ከሰራዊቱ የወጡና የሕይወት መስዋዕትነት የከፈሉ አባላት ቤተሰቦችን ማገዝ የመርሐ ግብሩ አካል መሆኑን ጠቁመዋል። 

በኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ፣ ባሕር ኃይል፣ የብሔራዊ ተጠባባቂ ኃይል የጦር ክፍሎች ከካምፓቸው ጀምሮ እስከ ተሰማሩበት አካባቢ ሁሉ የተለያዩ በጎ ተግባራትን ያከናውናሉ ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሰላም፣ ልማትና ክብር እንዲጠበቅ ሰራዊቱ ቀዳሚው ዋስትና መሆኑን ገልፀው፣ ሰራዊቱ ባለበት ሁሉ የደም ልገሳን ጨምሮ በመርሐ ግብሩ በጎ ስራውን እንዲያጎለብት ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም