ከሰራዊቱ የጀግንነትና የድል አድራጊነት ታሪክ ለሚቀዳው የመቻል ስፖርት ክለብ ህዝባዊ ድጋፉ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት - ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ - ኢዜአ አማርኛ
ከሰራዊቱ የጀግንነትና የድል አድራጊነት ታሪክ ለሚቀዳው የመቻል ስፖርት ክለብ ህዝባዊ ድጋፉ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት - ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 30/2016(ኢዜአ)፦ ከሰራዊቱ የጀግንነትና የድል አድራጊነት ታሪክ ለሚቀዳው የመቻል ስፖርት ክለብ ህዝባዊ ድጋፉ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ።
የመቻል ስፖርት ክለብ 80ኛ ዓመት የምስረታ በዓልን አስመልክቶ በአዲስ አበባ ስካይ ላይት ሆቴል የገቢ ማሠባሠቢያ(ቴሌቶን) በመካሄድ ላይ ይገኛል።
በዝግጅቱ ላይም ፊልድ ማርሻሉን ጨምሮ የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሀመድ፣ ከፍተኛ የፌዴራልና የክልል፣ የከተማ አስተዳደር የስራ ኃላፊዎች፣ የሠራዊቱ ከፍተኛ መኮንኖች፣ ባለሃብቶች፣ የብሔራዊ ስፖርት ፌዴሬሽንና ማኅበራት፣ የመቻል ስፖርት የቀድሞ ስፖርተኞች፣ አሰልጣኞች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው ግለሰቦች ታድመዋል።
በዚሁ የገቢ ማሰባሰቢያ መድረክ ላይ የተገኙት የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ባስተላለፉት መልዕክት ከሰራዊቱ የጀግንነትና የድል አድራጊነት ታሪክ ለሚቀዳው የመቻል ስፖርት ክለብ ህዝባዊ ድጋፉ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስገንዝበዋል።
የመቻል ስፖርት ክለብን ህዝባዊነት በማስጠበቅ ኢትዮጵያውያን ለክለቡ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው መቀጠል እንደሚኖርባቸውም ገልጸዋል።
ቀዳማዊ ኃይሥስላሴ ከ80 ዓመታት በፊት የጦር ሰራዊቱ የሞራል ስንቅ የሆነ የስፖርት ክለብ እንዲኖረው ለማስቻል ታሪካዊ አሻራ አሳርፈው አልፈዋል ብለዋል።
በአሁኑ ወቅትም የመከላከያ ሠራዊት የመቻልን የቀደመ ገናና ታሪክ በመመለስ ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የመከላከያ ሠራዊት ተቋማት ላይ በተወሰደ ተቋማዊ የማሻሻያ እርምጃ ከነበሩበት ውድቀት ተነስተው ወደ ስኬታማ የማምረት አቅም መሸጋገራቸውን አስታውቀዋል።
የመቻል ስፖርት ክለብም የኢትዮጵያ የስፖርት ክለቦች ሞዴል ሆኖ ሳለ ባለፉት 30 ዓመታት ባለቤት አልባና ስሙም ታሪክ ሆኖ እንደነበር ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅትም የመቻል ስፖርት ክለብን ከነበረበት ውድቀት በማውጣት፣ ስምና ታሪኩን በማደስ፣ የአመራር ቦርድ በማደራጀት፣ የቀጣይ መዳረሻ ራዕይ በመቅረጽና ልዩ ልዩ የማስተካከያ እርምጃ በመውሰድ በአጭር ጊዜ ወደ ስኬታማ የመነቃቃት ምዕራፍ መሸጋገሩን ገልጸዋል።
በአዲስ መልክ የተዋቀረው የክለቡ አመራር ቦርድ መቻል ስፖርት ቡድን በአጭር ጊዜ ተደራጅቶ ስኬት እንዲያስመዘግብ በማድረጋቸው አመስግነዋል።
የመቻል ስፖርት ክለብ የኢትዮጵያውያን ክለብ መሆኑን ጠቁመው ለዚህም የክለቡን ህዝባዊነት አስጠብቆ ለማስቀጠል ራዕይ ተነድፎ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
በዛሬው ዕለት በስካይ ላይት ሆቴል የገቢ ማሠባሠቢያ(ቴሌቶን) ስርዓት ላይ በመገኘት የገንዘብና የሞራል ድጋፍ ለማድረግ የታደሙ አካላትንም አመስግነዋል።
ከሰራዊቱ የጀግንነትና የድል አድራጊነት ታሪክ ለሚቀዳው የመቻል ስፖርት ክለብ ህዝባዊ ድጋፉ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ፊልድ ማርሻሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ64 ነጥብ የ2016 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዮን በሆነበት ዘመን የመቻል እግር ኳስ የስፖርት ቡድን 80ኛ ዓመቱን እያከበረ 63 ነጥብ በመሰብሰብ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል።
የገቢ ማሠባሠቢያ (ቴሌቶን) ዝግጅቱ መቻል ስፖርት ክለብን በማጠናከር በመጪዎቹ አምስት ዓመታት ከአፍሪካ ምርጥ 10 ክለቦች አንዱ የማድረግ ራዕይን የሰነቀ መሆኑም ተገልጿል።