ቀጥታ፡

መቻል ስፖርት ክለብ የጀግናው መከላከያ ሠራዊት የድል አድራጊነት አኩሪ ምልክት ነው - ኢንጂነር አይሻ መሀመድ 

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 30/2016(ኢዜአ)፦ መቻል ስፖርት ክለብ የጀግናው መከላከያ ሠራዊት የድል አድራጊነት አኩሪ ምልክት ነው ሲሉ የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሀመድ ገለጹ። 

የመቻል ስፖርት ክለብን 80ኛ የምስረታ ዓመት በዓልን አስመልክቶ በአዲስ አበባ የገቢ ማሰባሰቢያ (ቴሌቶን) በመካሄድ ላይ ይገኛል። 

በዝግጅቱም የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሀመድ፣ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣የድሬ ዳዋ ከንቲባ ከድር ጃሀር፣ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ የመከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ መኮንኖች፣ ባለሃብቶች፣ የብሔራዊ ስፖርት ፌዴሬሽንና ማኅበራት፣ የመቻል ስፖርት የቀድሞ ስፖርተኞች፣ታዋቂ የስፖርትና የኪነ-ጥበብ ሙያተኞች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው ግለሰቦች ታድመዋል። 

የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሀመድ በዚሁ ጊዜ ባስተላለፉት መልዕክት፥ መቻል ስፖርት ክለብ በተለያዩ ዓለም አቀፍ የስፖርት መድረኮች ኢትዮጵያን በኩራት ያስጠሩ ስፖርተኞችን ያፈራ ነው ብለዋል። 


 

ክለቡ የሠራዊቱ የድል አድራጊነት የሞራል ስንቅ በመሆኑ የብሔራዊ ኩራት ምንጭ ነው ብለዋል፡፡

የሠራዊቱን ህዝባዊነት ለማስቀጠል ስኬታማ የለውጥ እርምጃ በማድረግ የመቻል ክለብንም ወደቀደመ ገናና ክብሩ ለመመለስ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። 

ለዚሁ ስራ የሞራልና የገንዘብ ድጋፍ እያበረከቱ ለሚገኙ አካላትም ምስጋና አቅርበዋል። 

የመቻልን ክለብ ለማጠናከር እና በኢትዮጵያ ስፖርት ተሳትፎ  የበኩሉን አስተዋፅኦ ለማድረግ በሚደረገው የገቢ ማሰባሰቢያ  ላይም  ሁሉም የበኩሉን ድጋፍ እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል፡፡


 

የገቢ ማሠባሠቢያ (ቴሌቶን) ዝግጅቱ መቻል ስፖርት ክለብን በማጠናከር በመጪዎቹ አምስት ዓመታት ከአፍሪካ ምርጥ 10 ክለቦች የማድረግ ራዕይን እውን ለማድረግ ዓላማ ያደረገ መሆኑም ተገልጿል። 

የመቻል እግር ኳስ የስፖርት ቡድን በዘንድሮው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 63 ነጥብ በመሰብሰብ  ሁለተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል። 

የመቻል ስፖርት ክለብ የሀገር መከላከያ ሠራዊት የአሸናፊነት የድል ዓርማ ሆኖ ከሠራዊቱ በተውጣጡ ስፖርኞች በ1936 ዓ.ም የተመሰረተና ታዋቂ ስፖርተኞችን ለማፍራት የበቃ ስመ ገናና የስፖርት ክለብ መሆኑ ይታወቃል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም