በደብረ ማርቆስ ከተማ "ሠላም ለሁሉም ሁሉም ለሠላም" በሚል መሪ ሀሳብ በቀበሌ ደረጃ የተካሄደው የሠላም ኮንፍረንስ ተጠናቀቀ - ኢዜአ አማርኛ
በደብረ ማርቆስ ከተማ "ሠላም ለሁሉም ሁሉም ለሠላም" በሚል መሪ ሀሳብ በቀበሌ ደረጃ የተካሄደው የሠላም ኮንፍረንስ ተጠናቀቀ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 30/2016(ኢዜአ)፦ በደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር ከሁሉም ቀበሌ የማህበረሰብ ክፍሎች ጋር "ሠላም ለሁሉም ሁሉም ለሠላም" በሚል መሪ ሀሳብ ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የነበረው የሠላም ኮንፍረንስ ተጠናቀቀ።
በቀበሌ 03 ማጠቃለያ የሠላም ኮንፍረንስ ላይ የደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ መንበሩ ዘውዴ ተገኝተው መልዕክት አስተላልፈዋል።
በመልዕክታቸውም ጦርነት ሁሉንም የሚያጠፋ መንገድ ስለሆነ ችግሮችንና አለመግባባቶችን በውይይት መፍታት ይገባናል ብለዋል።
በክልላችን አልፎም በከተማችን በነበረው ጦርነት ኢኮኖሚው በከፍተኛ ደረጃ ማጎሳቆሉንና ከፍተኛ ሰብአዊና ቁሳዊ ኪሳራ ማድረሱን አስረድተዋል።
የሰላም ባለቤት መንግስትና የፀጥታ ሀይሉ ብቻ ሳይሆን ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል መሆኑን በውል በመረዳት የቀበሌው ማህበረሰብ ለህግ የበላይነት መረጋገጥና ለሰላም መስፈን መስራት ይጠበቅበታል ሲሉ አሳስበዋል።
የከተማችን አልፎም የክልላችን ህዝብ በየደረጃው በተፈጠሩ መድረኮች የገጠሙንን ችግሮች በሰላምና በውይይት መፍታት እንደሚገባ መንግስት ሀሳቡን ሲገልፅ ቆይቷል ብለዋል።
መንግስትም የህዝባችንን ጥያቄ በመቀበል ያጋጠሙንን ችግሮች ለመፍታት ስራዎችን እየሰራ ይገኛል ነው ያሉት።
በሁሉም ቀበሌዎች ሲካሄድ የቆየው የሰላም ኮንፍረንስ ባለ 5 ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ተጠናቋል ብለዋል።
በዚህም
1ኛ. በሰላምና በፀጥታ፣ በፓለቲካ፣ በማህበራዊ፣ በመልካም አስተዳደር፣ በማንነትና በራስ አስተዳደር ጉዳይ እንዲሁም የህገ - መንግስትን ስለማሻሻል እና ሌሎች ጥያቄዎችን አስመልክቶ እኛ የቀበሌ ነዋሪዎች ያነሳናቸውን ጥያቄዎች በየፈርጃቸው ለፌደራል መንግስትና ለክልሉ እንዲሁም የከተማ አስተዳደሩ መንግስት አካላት እንዲቀርብልን ስምምነት ላይ ደርሰናል፡፡
ሁሉም ጥያቄዎች በአንድ ጊዜ እንደማይመለሱ ስለምናምን መንግስት የህዝቡን ጥያቄ ለመፍታት ያለውን ቁርጠኝነት እንዲሁም በፍጥነት መመለስ ያለባቸውን ለመፍታት የሚኖረውን ዝግጁነት በጋራ እያየን እንዲሁም በሰላማዊ መንገድ እየተወያየን ጥያቄዎቹ እንዲፈቱልን መጠየቃችንን እንቀጥላለን፡፡
2ኛ. በክፍለ ከተማችን ውስጥ በርካታ የልማት ጥያቄዎች መኖራቸው ይታወቃል፡፡ እነዚህ የልማት ጥያቄዎች ያለ ሰላም ሊታሰቡ ስለማይችሉ ቅድሚያ በክፍለ ከተማችን ውስጥ ማንኛውም ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ የበኩላችንን ድርሻ ለመወጣት በውይይታችን የተስማማን መሆኑን እናሳውቃለን፡፡
3ኛ. በየደረጃው ያለ ህዝብ በርካታ ሁለንተናዊ ችግሮች ተጋርጠውበት ቆይተዋል፡፡ በርካታ ምስቅልቅሎችም ደርሰውበታል፡፡ ስለሆነም ይህን ዘርፈ ብዙ ችግር ተገንዝባችሁ ህዝቡን ወደ ሰላም የሚመልስና የቀበሌያችን ህዝብም ከሌሎች ወንድምና እህት ህዝቦች ጋር በጋራ በነፃነት ተዘዋውሮ እንዲሰራ ለማስቻል የድርሻችሁን እንድትወጠ ስንል እንጠይቃለን።
4ኛ. ታጥቃችሁ ጫካ የገባችሁ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን እንታገልለታለን የምትሉት ህዝብ ያለበትን ችግርና የህዝብ ህልውና እንዴት እንደተፈተነ በግልፅ ታውቃላችሁ፡፡
ስለሆነም ጥያቄያችሁን በሰላማዊ መንገድ በውይይትና በድርድር እንድታቀርቡ እንዲሁም የህዝባችሁን ስቃይ ለመቀነስ እንዲቻል መገዳደል ይብቃን ብላችሁ ወደ ወገኖቻችሁ እንድትቀላቀሉ የሰላም ኮንፈረንሳችን ተሳታፊ በሙሉ ወገናዊ ጥሪ እያስተላለፍን በየደረጃው ያለ የመንግስት መዋቅር ሆደ ሰፊ በመሆን እነዚህ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ጋር በመወያየት እና በመደራደር ለህዝባችን ሰላም ሲባል በይቅርታና በክብር እንድትቀበሏቸው ስንል እንጠይቃለን።
5ኛ. የከተማ አስተዳደር በምታገለግሉት ህዝብ ውስጥ የቀበሌያችን ተወላጆች እናንተን የመንግስት አስተዳደሮችን እና አብሮ ለዘመናት የኖረውን ወገኖቹን አምኖ እየኖረ መሆኑን በመገንዘብ የቀበሌያችን ህዝብ ተገቢውን አገልግሎት በመስጠት፣ ጥቃት እንዳይደርስበት፤ የልማት ጥያቄዎች እንዲመለሡለት በሰላም ኮንፈረንሳችን ጥሪያችንን እያስተላለፍን እኛም እንደቀደመው ሁሉ መደበኛ የልማትና መልካም አስተዳደር ስራዎች እንዲቀጥሉ እንደምንሰራ ቃል እንገባለን።