ቀጥታ፡

ዘላቂ ሰላምን በማረጋገጥ ዜጎችን ተጠቃሚ ያደረጉ ለውጦችን ለማስቀጠል በጋራ መስራት ይገባል-አቶ ብናልፍ አንዱዓለም

አዲስ አበባ፤ሰኔ 30/2016 (ኢዜአ)፦ዘላቂ ሰላምን በማረጋገጥ  ዜጎችን ተጠቃሚ ያደረጉ ለውጦችን ለማስቀጠል በጋራ መስራት እንደሚገባ የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዱዓለም ገለጹ፡፡

በአዲስ አበባ "ሰላም ለሁሉም፤ሁሉም ለሰላም" በሚል መሪ ሀሳብ አገር አቀፍ የሰላም ሩጫ ውድድር ተካሒዷል፡፡

ውድድሩ የተዘጋጀው በሰላም ሚኒስቴር እና በአጋር አካላት ትብብር ነው።


 

በመስቀል አደባባይ በተካሔደው ሩጫ የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዱዓለምንና የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤን ጨምሮ ሌሎች የፌደራል ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች፣ ታዋቂ አትሌቶችና የተለያዩ አገራት ዲፕሎማቶች ተገኝተዋል።

የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዱዓለም በዚሁ ወቅት፤ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በልማቱ ዘርፍ ትልልቅ ለውጦችን እያስመዘገበች ትገኛለች ብለዋል፡፡

በዚህም ዜጎች ከመቸውም ጊዜ በላይ የልማቱ ተቋዳሽ እየሆኑ መምጣታቸውን አመላክተዋል፡፡

አሁን ላይ እየተመዘገቡ ያሉ ለውጦችን በማስቀጠል፤ የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሰላም ከመቼውም ጊዜ በላይ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

ሰላም የሁሉም መሰረት ነው ያሉት ሚኒስትሩ ፤ የዛሬው የሰላም ሩጫ ዋና ዓላማም የሰላም ፍላጎታችንን ከፍ አድርገን ለማሳየት ነው  ብለዋል፡፡

ዛሬ የተደረገው የሰላም ሩጫ ስለ ሰላም ግንዛቤ መፍጠርና ዜጎች ለዘላቂ ሰላም የበኩላቸውን ኃላፊነት መወጣት እንዳለባቸው ለማሳሰብም ጭምር ነው ብለዋል።

በመሆኑም ዜጎች ለዘላቂ ሰላም በትብብር መስራት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።


 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው፣ በመዲናዋ ህዝብን በማሳተፍ  አስተማማኝ ሰላም ማስፈን መቻሉን ተናግረዋል።

ይህን ሰላም አስጠብቆ ለመዝለቅ ሁሉም የመዲናዋ ማህበረሰብ እያበረከተ ያለውን አስተዋጽኦ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል፡፡


 

ኢዜአ ያነጋገራቸው የውድድሩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው መንግስት ለሰላም እያሳየ ያለውን ቁርጠኝት እንደግፋለን፤ እናደንቃለን ለዘላቂነቱ ደግሞ የበኩላችን እንወጣለን ብለዋል፡፡

ሽክ ኢብራሔም ሐጂ ሰላም የሁሉም ነገር መሰረት መሆኑን ጠቅሰው፤ ለዘላቂ ሰላም  በትብብር መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ሰላምን መጠበቅ ለአንድ አካል ብቻ የሚተው ስራ ሳይሆን የእያንዳንዱ ዜጋ ኃላፊነት መሆኑን የተናገሩት ደግሞ  አቶ ሰይፈ ከበደ  እና ወይዘሮ ቆንጅት ጌታቸው ናቸው፡፡

በአገር አቀፍ  ደረጃ በተለያዩ  ከተሞች በተካሄደው የሰላም የጎዳና ላይ የሩጫ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች ተሳትፈዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም