የፀጥታ መዋቅሩ ከህዝቡ ጋር ተቀናጅቶ በመስራቱ በሲዳማ ክልል አስተማማኝ ሰላም ማስፈን ተችሏል - የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ  

ሀዋሳ፤ ሰኔ 30/2016(ኢዜአ)፦ የፀጥታ መዋቅሩ ከህዝቡ ጋር ተቀናጅቶ በመስራቱ በሲዳማ ክልል አስተማማኝ ሰላም ማስፈን መቻሉን የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አለማየሁ ጢሞቲዎስ ገለጹ።

''ሰላም ለሁሉም ሁሉም ለሰላም" በሚል መሪ ሃሳብ' ሀገር አቀፍ የሩጫ ውድድር በሀዋሳ ከተማም ዛሬ ተካሂዷል።


 

የሲዳማ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አለማየሁ ጢሞቲዎስ በዚሁ ወቅት ስፖርትን ለሰላም በመጠቀም ዜጎች ለሰላም ዘብ እንዲሆኑ የሩጫ ውድድሩ መነሳሳትን እንደሚፈጥር ገልጸዋል።

ዝግጅቱ በክልሉ ሰላምና ፀጥታ መዋቅሮች አስተባባሪነት ከሰላም ሚኒስቴርና ከስፖርት ዘርፎች ጋር  በቅንጅት መዘጋጀቱን ጠቁመዋል።

የፀጥታ መዋቅሩ ከህዝቡ ጋር ተቀናጅቶ በመስራቱ በሲዳማ ክልል አስተማማኝ ሰላም ማስፈን መቻሉን ጠቅሰው፤ ሰላሙን ዘላቂ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ውስጥ የክልሉ ህዝብ ተሳትፎውን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።

በተለይ በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ሀገራዊ ምክክሩ ወሳኝ በመሆኑ መላው የክልሉ ነዋሪዎች በንቃት እንዲሳተፉ አቶ አለማየሁ አስገንዝበዋል።

በውድድሩ ላይ የተገኙት የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ መኩሪያ ማርሻዬ በበኩላቸው ሰላም ለልማት፣ ለእድገትና ለመልካም አስተዳደር መስፈን ዋነኛ መሣሪያ ስለሆነ ሁሉም ሊጠብቀውና ሊንከባከበው ያስፈልጋል ብለዋል።


 

ሀዋሳ ሰላሟን አስጠብቃ የዘለቀች መሆኗን ጠቅሰው ይህንን ማስቀጠል ከተቻለ የከተማዋን ልማትና የህዝቦችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሚቻል አስታውቀዋል።

ከሩጫ ውድድሩ ተሳታፊዎች መካከል አቶ ወንድሙ ቶርባ በሰጡት አስተያየት ሀዋሳ የብሄር ብሄረሰቦች ከተማ እንደመሆኗ መጠን ሰላም ለእኛ ልዩ ትርጉም አለው ብለዋል።

ሁላችንም በነፃነት መንቀሳቀስ የምንችለው የተረጋገጠ ሰላም ሲኖር ነው ያሉት አስተያየት ሰጪው፤  ለአካባቢያችንና ለሀገራችን ሠላም በጽናት መቆም ይገባል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም