የኢትዮጵያ ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ ዛሬ ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ ዛሬ ይካሄዳል
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 30/2016 (ኢዜአ)፦ የ2016 ዓ.ም የኢትዮጵያ ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ በወላይታ ድቻና ኢትዮጵያ ቡና መካከል ዛሬ ይደረጋል።
የዋንጫው አሸናፊ በቀጣይ ዓመት ኢትዮጵያን ወክሎ በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ይሳተፋል።
የወላይታ ድቻና የኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ ከቀኑ 9 ሰዓት በአዲስ አበባ ስታዲየም ይከናወናል።
ወላይታ ድቻ በግማሽ ፍጻሜው ኢትዮጵያ መድንን 1 ለ 0 እንዲሁም ኢትዮጵያ ቡና ሃዋሳ ከተማን 2 ለ 0 በማሸነፍ ለፍጻሜው ጨዋታ ደርሰዋል።
በአሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ የሚመራው ወላይታ ድቻ በኢትዮጵያ ዋንጫ ግስጋሴው ደሴ ከተማ፣ ሀድያ ሆሳዕና፣ ቅዱስ ጊዮርጊስና ኢትዮጵያ መድንን አሸንፏል።
ክለቡ በውድድሩ ባደረጋቸው 4 ጨዋታዎች 11 ግቦችን ሲያስቆጥር 4 ጎሎችን አስተናግዷል።
ተጋጣሚው ኢትዮጵያ ቡና በዘንድሮው የኢትዮጵያ ዋንጫ ጉዞው ወልዲያ፣ ኮልፌ ቀራኒዮ ከተማ፣ ፋሲል ከነማና ሃዋሳ ከተማን ማሸነፍ ችሏል።
በነጻነት ክብሬ የሚሰለጥኑት ቡናማዎቹ በ4ቱ ጨዋታዎች 12 ጎሎችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፉ የተቆጠረባቸው 1 ግብ ብቻ ነው።
የሁለቱ ክለቦች በርከት ያሉ ደጋፊዎች ለጨዋታው ተጨማሪ ድምቀት ይሰጡታል ተብሎ ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ ዋንጫን የሚያሸንፈው ክለብ በቀጣዩ ዓመት ኢትዮጵያን ወክሎ በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ይሳተፋል።
በተጨማሪም የውድድሩ አሸናፊ ክብደቱ 9 ነጥብ 4 ኪሎ ግራም፣ 40 ሴንቲ ሜትር ርዝመት ያለው እንዲሁም ከአልሙኒየምና ነሐስ የተሰራ ዋንጫ ይበረከትለታል።
145 ሺህ ብር ወጪ የተደረገበትን ዋንጫ የሰራው የመከላከያ ሰራዊት ፋውንዴሽን ነው።
የ2016 የኢትዮጵያ ዋንጫ በስድስት ዙር የተካሄደ ሲሆን 46 ክለቦች ተሳትፈዋል።
በ1937 ዓ.ም የተጀመረው የኢትዮጵያ ዋንጫ የ79 ዓመት ታሪክ ያለው አንጋፋ ውድድር ነው።