አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በ2017 የትምህርት ዘመን ተማሪዎችን በራሱ የቅብላ ፖሊሲ ያስተናግዳል - ኢዜአ አማርኛ
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በ2017 የትምህርት ዘመን ተማሪዎችን በራሱ የቅብላ ፖሊሲ ያስተናግዳል

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 29/2016(ኢዜአ)፦ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በ2017 የትምህርት ዘመን ተማሪዎችን በራሱ የቅብላ ፖሊሲ መሠረት በማድረግ በራሱ መስፈርትና መመዘኛ እንደሚቀበል ገለጸ።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 74ኛው የምርቃት ሥነ-ሥርዓት በሚሊኒየም አዳራሽ አካሂዷል።
በምርቃት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የዩኒቨርሲቲው የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ፍሬህይወት ታምሩ፣ የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የተመራቂ ቤተሰቦችን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
በመጀመሪያ፣ በሁለተኛና በሦስተኛ ዲግሪ በድምሩ 5 ሺህ 574 ተማሪዎች ለምርቃት በቅተዋል።
የትምህርት ሚኒስትርና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቻንስለር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ መንግሥት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በርካታ የለውጥ ሥራዎችን እየሰራ ነው።
ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲው ቆይታቸው የሥነ-ምግባርና ሙያቸውን የሚያዳብሩበት ሥልጠናዎች እንዲሁም የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተና አሠራር መጀመሩ ከለውጥ ሥራዎች መካከል መሆኑን ጠቅሰዋል።
ዩኒቨርሲቲዎች በምርምር፣ በመማር ማስተማር እንዲሁም በማኅበረሰብ ተኮር አገልግሎት የበለጠ እንዲጠናከሩ ራስ ገዝ እንዲሆኑ የሚያስችል አሠራር መዘርጋቱንም ተናግረዋል።
በዚሁ መሠረት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያው ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ መሆን መቻሉን ገልፀዋል።
ፕሮፌሰሩ አክለውም፤ ተመራቂዎች ዓለም በርካታ ፈተና ውስጥ እየገባች መሆኑን በመገንዘብ ፈተናውን ለመጋፈጥ ዝግጁ መሆን አለባችሁ ብለዋል።
የጋራ ችግሮቻችንን በአንድነት መጋፈጥና መፍታት ጊዜው የሚጠይቀው ጉዳይ መሆኑን መገንዘብ አለባችሁ፤ አገር ከእናንተ ብዙ ትጠብቃለች ሲሉም ገልፀዋል።
ተመራቂ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲው ቆይታቸው የቀሰሙትን እውቀትና ክህሎት ሥራ ላይ በማዋል ለአገርና ማኅበረሰብ ለውጥ መሥራት እንደሚጠበቅባቸውም አስገንዝበዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ዩኒቨርሲቲው በዛሬው ዕለት በቅድመ-ምረቃ 2 ሺህ 737 እና በድኅረ-ምረቃ መርኃ-ግብር 2 ሺህ 837 ተማሪዎች በድምሩ 5 ሺህ 574 ተማሪዎች ለመመረቅ በቅተዋል ብለዋል።
ባለፉት አሥር ወራትም ዩኒቨርሲቲው ስትራቴጂያዊ ዕቅድ ማውጣቱን ጠቁመው፤ አዲስ የሴኔት ሕግና መመሪያዎችም መዘጋጀቱንም አብራርተዋል።
ከቀጣዩ 2017 ዓ.ም ጀምሮ ዩኒቨርሲቲው በራሱ የቅበላ ፖሊሲ ተማሪዎችን መቀበል እንደሚጀምርም አስታውቀዋል።
ለዚህም በአገር አቀፍ ደረጃ የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ውጤት ያመጡ ተማሪዎች ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከመግባታቸው በፊት ተጨማሪ መመዘኛዎች በዩኒቨርሲቲው እንደሚሰጥ አስረድተዋል።
ከዩኒቨርሲቲው ሜዲካል ራዲዮሎጂ ትምህርት ክፍል 3 ነጥብ 98 በማምጣት በማዕረግ የተመረቀው ወጣት ብሩክ ምትኩ፤ በቀሰምኩት ዕውቀት አገሬን ለማገልገል ተዘጋጅቻለሁ ብሏል።
በዩኒቨርሲቲ ቆይታው የሚድዋይፈሪ ትምህርትን ያጠናው ተመራቂ ኤሊያስ ገበቶ በበኩሉ፤ የእናቶችን ጤና ለመጠበቅ በሚደረገው ጥረት በሙያዬ ለማገዝ ዝግጁ ነኝ ሲል ተናግሯል።