ብልፅግና ፓርቲ በአራት ክልሎች በተካሄደው የድጋሜና የቀሪ ምርጫ አብዛኞቹን መቀመጫዎች አሸነፈ - ኢዜአ አማርኛ
ብልፅግና ፓርቲ በአራት ክልሎች በተካሄደው የድጋሜና የቀሪ ምርጫ አብዛኞቹን መቀመጫዎች አሸነፈ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 29/2016(ኢዜአ)፦ ብልፅግና ፓርቲ በአራት ክልሎች በተካሄደው የድጋሜና የቀሪ ምርጫ ለክልልና ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አብዛኞቹን መቀመጫዎች ከፍተኛ ድምፅ በማግኘት አሸናፊ ሆነ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የ6ኛው ዙር በተለያዩ ምክንያቶች ምርጫ ባልተካሄደባቸው በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በአፋር፣ በሶማሌና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች ሰኔ 16 ቀን 2016 ዓ.ም የድጋሚና የቀሪ ምርጫ ማካሄዱ ይታወሳል።
ቦርዱ ዛሬ የድጋሚና ቀሪ ምርጫ ውጤት ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ይፋ አድርጓል።
ይህንንም ተከትሎ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተካሄደው ምርጫ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፤ ብልፅግና 4፣ ቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ 1 እንዲሁም የጉሙዝ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ 1 መቀመጫ አሸንፈዋል።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለክልል ምክር ቤት ደግሞ ብልፅግና ፓርቲ 60፣ ቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ 3 እና የጉሙዝ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ 8 መቀመጫ አሸንፈዋል።
በአፋር ክልል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፤ ብልጽግና ፓርቲ 2 እና ለክልል ምክር ቤት 27 መቀመጫዎችን በማግኘት አሸንፏል።
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ለክልል ምክር ቤት 3ቱንም መቀመጫዎች ብልፅግና ፓርቲ ማሸነፉ ተገልጿል።
በሶማሌ ክልል በተካሄደው የክልል ምክር ቤት ምርጫ 7 መቀመጫዎችን ብልጽግና ፓርቲ አሸንፏል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ ውብሸት አየለ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ የድጋሚና የቀሪ ምርጫ ሂደት የተሳካ እንዲሆን ቁሳቁስ ከማሟላት ጀምሮ በርካታ ሥራ ተሰርቷል ብለዋል።
መራጮች እውቀትን መሠረት በማድረግ እንዲመርጡ ግንዛቤ የማስጨበጥና ምርጫውን ለሚያስፈፅሙ አካላት ተገቢው ሥልጠና መሰጠቱንም ነው ያስረዱት።
ይህንንም ተከትሎ የድጋሜና የቀሪ ምርጫ በአራት ክልሎች፣ በ29 የምርጫ ክልሎችና በ 1 ሺህ 218 የምርጫ ጣቢያዎች መካሄዱን አስረድተዋል።
የምርጫ ሂደቱም ነፃ፣ ገለልተኛና ተዓማኒ እንደነበር ተናግረዋል።
የድጋሜና የቀሪ ምርጫ በተካሄደባቸው በአራቱም ክልሎች የመራጮች ተሳትፎ 85 በመቶ እንደነበር ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ፤ ቦርዱ የድጋሚና የቀሪ ምርጫን ለማካሄድ ጥናትን መሠረት ያደረገ ዝግጅት አድርጎ ወደ ሥራ መገባቱን ተናግረዋል።
በዚህም የምርጫ ክልል ጣቢያዎችንና ጽህፈት ቤቶችን በማቋቋም እንዲሁም በቂ ዝግጅት በማድረግ ምርጫውን ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ በታቀደው ጊዜ ማካሄድ እንደተቻለ ገልፀዋል።
በምርጫው 12 የፖለቲካ ፓርቲዎችና 12 የግል ዕጩዎች መሳተፋቸውን ያስታወሱት ሰብሳቢዋ ምርጫውም ከፍተኛ የሆነ ፉክክር የተካሄደበት እንደነበር አስታውሰዋል።
በምርጫው ከዚህ በፊት ተሳትፈው የማያውቁ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተሳተፉበት መሆኑንም ጠቅሰዋል።
የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የውጭና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ኃላፊ መብራቱ አለሙ (ዶ/ር) ድጋሚና የቀሪ ምርጫ ለገዥው ፓርቲና ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ለቀጣይ ትምህርትና ልምድ ሰጥቶ ማለፉን ተናግረዋል።
ምርጫው አንዳንድ ችግሮች ቢኖሩበትም ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ መካሄዱን በመግለፅ በምርጫው አሸናፊ የሆነው ፓርቲም የሕዝብ ጥያቄዎችን ለመመለስ ተግቶ መሥራት እንደሚገባው አመላክተዋል።
የጉሙዝ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ጉህዴን) ሊቀ-መንበር ግራኝ ጉደታ፤ ፓርቲያቸው ከተመሠረተ ወዲህ በአሁኑ ምርጫ ለሁለተኛ ጊዜ መሳተፉን ተናግረዋል።
የአሁኑ ምርጫ ፍፁም ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ በመካሄዱ መደሰታቸውን ጠቅሰው፤ ምርጫ ቦርድ በገለልተኛነት ማገልገሉ የሚደነቅ ነው ብለዋል።